አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የማንሠራራት ዘመን እውን መሆኑን የሚያበስሩ በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመከወን ላይ ትገኛለች፡፡
ከእነዚህም መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በከተሞች የተሰራው የኮሪደር ልማትና በርካታ ሜጋ ብሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት ባሻገር ግንባታቸው በፍጥነትና በላቀ ጥራት በመከወን ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የቢሾፍቱ ዓለም ዓቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ይገኝበታል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ግዙፉ እና ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ ያለ የአየር መንገድ እንደመሆኑ መጠን፣ የማስፋፊያ ዕቅዶቹን ለማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊና ግዙፍ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ያስፈልገዋል።
ይህንን ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ፍላጎት መሠረት በማድረግ በኦሮሚያ ክልል፣ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በስተደቡብ ምስራቅ በኩል የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ኢትዮጵያ የማንሠራራት ጉዞዋን ለማቀላጠፍ ታላላቅ ትልሞችን ወደ ተግባር ማምጣት እንዳለባት ያሳየው ይህ ፕሮጀክት÷የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እድገት ለማሳለጥ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡
አየር መንገዱ ሀገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን ዘላቂ ሞተር ይሆናል። የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በሀገር ውስጥ ምርት እድገት፣ በውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና በውጪ ምንዛሪም ማሳደግን ያስችላል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው በሚሊየን የሚቆጠሩ መንገደኞችን እና በሚሊየን የሚቆጠር ቶን ጭነት ማስተናገዱ በራሱ ለሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ቀጥተኛ እና ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል።
የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ መጠናቀቅና ስራ መጀመር፤ ቢሾፍቱ ከባህር ወለል በላይ ያላት ከፍታ ከአዲስ አበባ አነስተኛ በመሆኑ፣ አውሮፕላኖች በሚነሱበትና በሚያርፉበት ወቅት ያነሰ ነዳጅ እንዲጠቀሙና ከፍተኛ የጭነት አቅም (Payload) እንዲይዙ ያስችላቸዋል።
ዋነኛው ጉዳይ ደግሞ በዓመት እስከ 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። በዚህም በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አስር አንዱ፤ ከአህጉሪቱ አፍሪካ ደግሞ ቁጥር አንዱ ግዙፍ አውሮፕላን ያደርገዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው የተሳፋሪዎች ማስተናገጃ ብቻ ሳይሆን፣ ኢሚግሬሽንና የጉምሩክ አገልግሎቶች፣ ዘመናዊ ገበያዎች፣ የኮንፈረንስ ማዕከላት፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ባለ ኮከብ ሆቴሎች እና የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ አነስተኛ ከተማ ይሆናል።
ፕሮጀክቱ ለብዙ ሺህ የማሕበረሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን÷ ሥራ ሲጀምር ደግሞ በአቪዬሽን፣ በቱሪዝም፣ በሆቴል እና በትራንስፖርት ዘርፎች በርካታ የሥራ ዕድሎችን እንደሚከፍት ይጠበቃል።
የቢሾፍቱ ከተማን የተፈጥሮ ሐይቆች እና የቱሪዝም መስሕቦች ከዓለም አቀፍ መንገደኞች ጋር በማስተሳሰር የሀገሪቱ እድገት ምሰሶ የሆነውን ቱሪዝም በማሳደግ ከፍተኛ ገቢን ያስገኛል፡፡
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከባሕር ጠለል በላይ በ1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ ከአዲስ አበባ ቦሌ (2 ሺህ 334 ሜትር) በተሻለ ለአውሮፕላኖች መነሳትና ማረፍ እጅግ ምቹ የአየር ሁኔታን ይሰጣል።
ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአህጉረ አፍሪካ ያላትን የአቪዬሽን የበላይነት የበለጠ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ አህጉሪቱን ከሌሎች አህጉራት ጋር የሚያገናኝ የአቪዬሽን ማዕከል ይሆናል፡፡
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ፣ የአቅም እና የአገልግሎት ደረጃ የሚያሸጋግር የማንሠራራት ዘመን የታሪክ ማዕዘን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ትናንት “ኢትዮጵያ ተነሥታለች” ስንል ምኞት ሳይሆን ዛሬ በተጨባጭ ያረጋገጥነው እውነት ነው፤ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማማ እስከ ዘመናዊው የኮሪደር ልማት፣ ከቢሾፍቱ ሜጋ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ድረስ ሀገራዊ መነቃቃታችን በተግባር ተመስክሯል።
ስለሆነም ከእንግዲህ ወደኋላ አንመለስም፤ በጀመርነው ታሪካዊ የማንሠራራት ጉዞ የልማት ኃይላችንን ይበልጥ በማፋጠን የኢትዮጵያን ትንሣኤ ወደ ዘላቂ ብልጽግና ከፍ እናደርጋለን እንጂ።
በመልካም ፈቃዱ

