አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለመጪው አዲስ ዓመት በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እየቀረቡ ነው፡፡
ፋና ዲጂታል በላፍቶ ሁለገብ ገበያ ማዕከልና ሌሎች አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት ÷ ለዘመን መለወጫ በዓል መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በበቂ ሁኔታ ለሸማቹ ሕብረተሰብ ተደራሽ እየሆኑ ነው፡፡
ነዋሪዎች ለበዓል የሚሆኑ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በተዘጋጁ ማዕከላት ያለ ምንም እንግልት ሲሸምቱም መመልከት ተችሏል፡፡
ፋና ዲጂታል ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ÷ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ከመላው ሀገሪቱ በበቂ ሁኔታ እየገባ እንደሆነና ለበዓሉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከወትሮው በተለየ መልኩ የንግድ እንቅስቃሴው እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአቅርቦት ችግር ባለመኖሩ ምክንያትም ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ነው ያመላከቱት፡፡
ሸማቾች በበኩላቸው÷ ለአዲስ ዓመት እና በመጪው መስከረም ለሚከበሩ በዓላት ያለው የመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዓላቱን ምክንያት በማድረግ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊውን ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ÷ መጪውን የአዲስ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ከክልሎች እና ከአጎራባች ከተሞች ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
በየደረጃው የሚከናወኑ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከልና የገበያ ማረጋጋት ሥራን ለማከናወን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን አመልክቷል፡፡
ስለሆነም የከተማዋ ነዋሪዎች ሕገወጥ የሆነ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማቸው በ8588 ነፃ የስልክ ጥሪ መስመር በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በመልካም ፈቃዱ

