አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ለአዲሱ ዓመት በዓል ከ4 ሺህ 500 በላይ የቁም እንስሳት እርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሚሽነር አሕመድ መሃመድ÷ ለመጪው አዲስ ዓመት በዓል ከ4 ሺህ 500 በላይ የቁም እንስሳትን እርድ ማከናወን የሚያስችል አጠቃላይ ዝግጅት ተጠናቅቋል ብለዋል።
በአዲሱ ዓመት በዓል ከ3 ሺህ በላይ በሬዎች እና ከ1 ሺህ 500 በላይ በግና ፍየሎች እርድ ለመከወን መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ በግና ፍየልን በ300 ብር፣ በሬዎችን ደግሞ በ2 ሺህ 100 ብር የቄራ የእርድ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል።
ዜጎች ስጋ ለመግዛት ወደ ልኳንዳ ቤቶች ሲያመሩ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የታረደ መሆኑንና ስጋው ላይ የማረጋገጫ ማሕተም መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ማሳሰባቸውንም ድርጅቱ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

