Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአንጋፋዋ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ በአምቦ ከተማ ይፈጸማል

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ሥራዎቿ የምትታወቀው የአንጋፋዋ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ቀብር ሥነ ሥርዓት በነገው ዕለት በአምቦ ከተማ ይፈጸማል።

ለበርካታ ዓመታት በተለይም በትግል ዘፈኖቿና በግጥሞቿ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ትግል በማቀንቀን የምትታወቀው አርቲስት እልፍነሽ ሥርዓተ ቀብር በአምቦ ከተማ እንደሚፈጸም አዘጋጅ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የአርቲስቷ አስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር በነገው ዕለት ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ድረስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል፡፡

ከሽኝት መርሐ ግብሩ በኋላ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ በሕይወት እያለች ‘ከዚህ ዓለም ስሰናበት ቀብሬ አምቦ ይሁን’ ባለችው ኑዛዜ መሠረት ወደ አምቦ ሽኝት እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡

በአፋን ኦሮሞ ሙዚቃዎቿ የምትታወቀው አንጋፋዋ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ ይታወሳል፡፡

ተወዳጇ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ለበርካታ ዓመታት በተለይም በትግል ዘፈኖቿና በግጥሞቿ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ስትታገል ቆይታለች።

አርቲስቷ የጥበብን ኃይል በመጠቀም በሕዝባዊ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና በመጫወት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ድምጻውያን መካከል ትጠቀሳለች።

Exit mobile version