Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጽናት ቀን የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ነገ ጳጉሜን 3 የጽናት ቀን በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል።

በቀኑ የመከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያከናወኗቸው ተግባራት ይዘከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ÷ ዕለቱን ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቁን ጠቁመው÷ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በጽናት በመመከት ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም መረጋገጥ መሠረት መሆኑንም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስም የሰላም ዘብ በመሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው ÷ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ሕገወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ ተጠቃሽ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሀገሪቱ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን በብቃት በመመከት የሀገር አለኝታነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ በማድረግ ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትም የኢትዮጵያ ዲጂታል ጉዞ እንዲሳለጥ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምሕዳር ግንባታ ላይ ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

Exit mobile version