Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበች ነው – አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች አሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር።

የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የጽናት ቀንን “ጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እያከበሩ ይገኛሉ።

በመርሐ ግብሩ ላይ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሥራ እንቅስቃሴዎች ተዘክረዋል።

አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የኢትዮጵያን የጽናት ጉዞ የሚያሳይ ነው፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መካሄዱን ያወሱት አፈጉባኤው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በስኬት መጠናቀቃቸው የኢትዮጵያውያን የጽናት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ይህ ሀገራዊ የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ እንዳይሳካ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ መሰል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የማይናወጥ ብሔራዊ አንድነት፣ ጠንካራ ሀገራዊ መግባባትና ትስስር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ወጣቱ ትውልድ የቀደሙ አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩለትን ሀገር በጽናት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version