አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ፈተናዎች ያፀኗት ሀገር በመሆኗ ፈተናዎችን ይበልጥ ወደ ዕድል በመቀየር ትሻገራለች አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፡፡
ጳጉሜን-3 የጽናት ቀን ”ፅኑ መሠረት ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
አቶ አወል አርባ በዚሁ ወቅት ፥ የጽናት ቀንን ስናከብር ለሀገር ሉዓላዊነት የተከፈለውን መስዋትነት የምንዘክርበት ቀን በመሆኑ በፅናት እንቆማለን፣ታሪክን እናስቀጥላለን፣አሰባሳቢና አሻጋሪ የድል ታሪክን ደጋግመን እንዘክራለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፈተናዎች ያፀኗት ሀገር በመሆኗ ፈተናዎችን ይበልጥ ወደ ዕድል በመቀየር ትሻገራለች ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሀገራዊ ምክክር ያሳካነው ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ጉዞ የፖለቲካ ጥያቄ ላላቸው አካላት ሁልጊዜም ለውይይት በሩ ክፍት መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላም የመጠበቅና የማረጋገጥ ስራ የፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች በመሆኑ በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

