አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንጋፋዋ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ሥርዓተ ቀብር በአምቦ ከተማ ተፈጽሟል፡፡
የአርቲስት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እልፍነሽ ቀኖ ሥርዓተ ቀብር ወዳጅ ዘመድ፣ አድናቂዎቿ እና የአምቦ ከተማና አከባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ነው የተፈጸመው፡፡
ተወዳጇ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ለበርካታ ዓመታት በተለይም በትግል ዘፈኖቿና በግጥሞቿ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ስትታገል ቆይታለች።
አርቲስቷ የጥበብን ኃይል በመጠቀም በሕዝባዊ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና በመጫወት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ድምጻውያን መካከል ትጠቀሳለች።
የኦሮሞ ሴቶች የጀግንነትና የጽናት ምልክት የሆነችው እልፍነሽ ቀኖ÷ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው “ሲቡ ጉቶ” በተባለች ስፍራ በ1954 ዓ.ም ነበር የተወለደችው።
አርቲስት እልፍነሽ በ1969 ዓ.ም ወደ ትግል በመቀላቀል ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሥነ ጥበብ ሥራዎቿ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች።
አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የሁለት ሴት ልጆች እናት ነበረች።

