Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአዲስ ዓመት በዓል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሰርቷል – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሰርቷል አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓል የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስና ድንገተኛ ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ ተሰርቷል፡፡
በበዓሉ ዋዜማና በበዓሉ ዕለት ሊከሰቱ የሚችሉ የኃይል መቆራረጦችን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተቋሙ መዋቅሮች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት የተደራጀ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
እስከ በዓሉ ዕለት ድረስ 24 ሰዓት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የቴክኒክ ቡድን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመቀናጀት ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በሁሉም የአገልግሎቱ ሪጅኖችና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አጣዳፊ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጁ የጥገና ቡድኖች መደራጀታቸውን አመልክተዋል።
በበዓሉ ዋዜማ ሊፈጠር የሚችለውን ተጨማሪ ኃይል ለመቋቋም 178 ትራንስፎርመሮች አቅማቸው የተሻሻለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ 88ቱ በአዲስ አበባ እና 90ዎቹ በክልል ከተሞች የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በበዓሉ ወቅት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለማመጣጠን ደንበኞች ኃይል ቆጣቢ ቁሳቁሶችን እንዲጠቀሙና የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶቻቸው ለአደጋ የማያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ደንበኞች በበዓሉ ወቅት ድንገተኛ የኤሌክትሪክ አደጋ ሲያጋጥማቸው ወይም የጥገና ጥቆማና አስተያየት ለመስጠት 905 በመደወል በነጻ ማሳወቅ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
Exit mobile version