አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በክልሉ ባህላዊ እሴቶችን በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዘንድሮው የጓንዷ በዓል ማጠቃለያ ፕሮግራም በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ጓንዷ የጨለማ ወቅት ታልፎ መጪው አዲስ ዓመት የሰላምና የደስታ እንዲሆን የተስፋ መቀበያ ነው፡፡
ጓንዷ የጉሙዝ ብሔረሰብ ብቻ ሳይሆን፤ የክልሉም የሀገርም ሀብት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በጉሙዝ ብሔረሰብ ግጭትን የሚፈቱ ሰላምን የሚያጠናክሩ አኩሪ እሴቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ የክልሉ መንግሥት ባህላዊ እሴቶችን በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
ጓንዷ ከኅብር ቀን ጋር በጥምረት መከበሩ አብሮነትን ለማጠናከር ትልቅ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዓሉ በድምቀት እንዲከበር የታየው መተባበርና መደጋገፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

