አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ውስጥ የኅብረት፣ የአንድነት እና የጋራ ጽናት ጥበብ ሁልጊዜም የማይበገር የድል መሠረት ሆኖ አልፏል።
አባቶቻችን «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» ብለው እንደተረቱት፣ ኢትዮጵያውያን በአንድ ዓላማና በጋራ ልብ ሲቆሙ የማይቻለው ተችሎ፣ የማይታለፈው የፈተና ጋራና ሸንተረር ሁሉ ሜዳ ሆኗል።
የአንድነትና የኅብረት ኃይል ለሀገር ሕልውናና ለከፍታ የሚሰጠውን ዋጋ እኛ ብቻ ሳንሆን አፍሪካውያንም በደምብ ይገነዘቡታል።
የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ÷ «አንድነት ለነፃነትና ለዕድገት ዋነኛው መሠረት ነው፤ በኅብረት የሚቆም ሕዝብ የማያልፈው ፈተና የለም» ሲሉ የጋራ ጥረትን አስፈላጊነት ገልጸውታል።
እንዲሁም ለጥቁሮች ነጻነት ዘብ በመቆም የሚታወቀው አሜሪካዊ የሲቪል መብቶች ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ዶ/ር) ÷ «በአንድነት አብረን መኖርን ካልተማርን፣ በብቸኝነት እንደ ሞኞች እንጠፋለን» በማለት ነበር የኅብረትን ወሳኝነት ያጎላው።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራትና የተስፋ ብርሃን ሆና እንድትቆም ያደረጋት ይህ የማይበገር የሕዝቦቿ ሕብረት ነው።
ታላቁ የዓድዋ ድል የዚህ ኅብረት ታሪካዊ ውጤት ነው፤ ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው በአንድነት ዘምተው የቅኝ ገዢዎችን እሳቤ የሰበሩትና የነፃነታችንን ዓለም አቀፍ አርማ ያቆሙት በዚሁ የጋራ ጥንካሬ ነው።
ይህ መሠረቱ ከማይናጋው የዓድዋ ድል የተቀዳ የኅብረት መንፈስ ዛሬም አልጠፋም። ምንም እንኳን በተለያዩ ዘመናት የኅብረታችን ገመድ የላላ፣ የአንድነታችን መሠረት የሳሳ መስሎ የሚታያቸው ወገኖች ቢኖሩም፣ የዚያ ትውልድ ወርቃማ ውርስ ዛሬም አዳዲስ የታሪክ ድሎችን መውለድ ችሏል።
ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መስካሪ በመሆን በጋራ ያቆሙት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የዚህ ዘመናዊ ኅብረት ሕያው ምስክር ነው።
ዛሬ ጳጉሜን 4 «የኅብር ቀን» ተብሎ ሲሰየም፣ የጋራ ድክመታችንን በኅብረት በማሸነፍ የሕዳሴውን ግድብ ምረቃ አብረን ያበሰርንበትን ዕለት እያከበርን ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሚሊየኖች ዜጎች ተመው በአጭር ጊዜ ውስጥ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለአካባቢ ጥበቃና ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያሳዩት አስደናቂ ተሳትፎ የኅብረታችን ሌላው ታላቅ ትሩፋት ነው።
በየዘመናቱ ሀገርን የሚፈታተኑ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮች፣ ከጦር የበለጡ የውስጥና የውጭ ጫናዎች ሁሉ ሊቋቋሙ የተቻለውና ወደፊትም የሚቻለው በኅብረት በመቆም ብቻ ነው።
ኅብር ሲደረጅ ሀገርን ማቆም፣ ከፍታ ላይ ማውጣትና የታሪክ አቅጣጫን ወደ በጎ መቀየር ቀላል ይሆናል።
በታሪኩ ለገሰ

