Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በብዝኃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በብዝኃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል አሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ።
ጳጉሜን 4 የህብር ቀን ‘ኢትዮጵያ በህብር ቀለም የተፃፈች ሀገር’ በሚል መሪ ሃሳብ በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እንዳሉት፤ በክልሉ አብሮነትና አንድነትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛና በኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የደመቀች ሀገር መሆኗን ገልጸው ብዝኃነትን በማቀናጀት ዘርፈ ብዙ ልማቶችን ማሳካት ይገባል ብለዋል።
በብዝኃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ በማንሳት ለዚህም አዲሱ ትውልድ ከእኔነት ይልቅ ‘እኛነትን’ በማስቀደም የጋራ ትርክትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የህብር ቀንን ማክበሩ ብዝኃነትን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትንና የወል ትርክቶችን የሚያጠናክር መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሯ በአዲሱ ዓመትም በህብረትና በአንድነት በመቆም ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የህብር ቀንን ማክበሩ ብዝሃነትን፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትንና የወል ትርክቶችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሯ አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት የፓናል ውይይትና የደም ልገሳ ሥነ ስርዓት መካሄዱን የዘገበው ኢዜአ ነው።
Exit mobile version