Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የትውልድ ብርሃን

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዓድዋ የነጻነት አደባባይ እስከ ህዳሴው ግድብ ሜጋ ፕሮጀክት ድረስ ያለው ብሔራዊ ጉዞ በተለያዩ ዘመናትና የታሪክ አውዶች የተከናወነ ነው፡፡
የዛሬው የልማት ስኬታችን ከቀደሙት ትውልዶች ዘመናትን ከተሻገረ ትግል፣ ከተማሩት መራር ትምህርት እና ካካበቱት ታሪካዊ ልምድ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።
ከ1818 እስከ 2017 ዓ.ም የሚዘልቀው የሀገራችን የታሪክ ምዕራፍ አንድ ወጥ የሆነ ማዕከላዊ ሀሳብን ያስተላልፋል፤ ይኸውም “ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የራሷን ዕድል የመወሰን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ብቃት አላት” የሚል ነው።
አባይ ለኢትዮጵያ ተራ የውሃ ሀብት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ትውልድ ከትውልድ፣ መንግሥት ከመንግሥት የተሸከመው ሕያው የልማትና የፍትሕ ጥያቄ እንጂ።
አባይን ከተፈጥሯዊ ሀብትነት አልፎ ወደ ተጨባጭ የልማትና የኢኮኖሚ ምንጭነት መቀየር አቅቶት፣ በእንጉርጉሮና በቆሞ ቀር ዜማዎች ብቻ “የማይበላ ፍሬ” ሆኖበት ዘመን ዘመንን እየወለደ እስከዚህኛ ትውልድ ደርሷል።
ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ናይል ታሪካዊ ቅኝት” በተሰኘው ጽሑፋቸው እንደሚያስረዱት፤ ከነገሥታቱ መካከል አጼ አምደ ጽዮን (1314 – 1344) በወቅቱ ከግብፅ ጋር ለነበረው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ውጥረት እንደ አይነተኛ መደራደሪያ የአባይን ወንዝ ፍሰት የማዞር ሀሳብን በዲፕሎማሲያዊ ጫናነት ይጠቀሙበት ነበር።
ሆኖም ያ ሀሳብ በወቅቱ ቢፈጸም እንኳ የኢትዮጵያን የጂኦ-ፖለቲካዊ ዕምባ መንገድ ይቀይር እንደሆን እንጂ ከዓይናችን የሚፈሰውን የድህነት ዕንባ የሚያብስ አልነበረም። የወንዙን ሀብት ከተፈጥሮ እጣ ፋንታነት አሻግሮ ለኢኮኖሚ ጉልበትነት ማዋል አልተቻለም ነበር።
ጥያቄው ግን ከነጻነትና ከሀገር ህልውና ጋር ሲያያዝ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። የራሷን ሀብት ከልክሎ ሀገር እንዳትበለጽግ ያፈጀውና በ1880ዎቹ በአፍሪካ የተንሰራፋው የቅኝ ግዛት እሳቤና ወረራ በሀገራችን ላይ ሲመጣ፣ የኢትዮጵያ የአንድነት ክር ጠነከረ፤ ለድል በአንድነት ተመሙ።
ያልደፈር ባይነትና የመቻል አቅም በትውልዱ ብዕርና ደም ዳግም ሊጻፍ፣ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ሊከፈት ግድ ሆነ።
የዓድዋ የአንድነት ትምህርት በልማት ሥራ ውስጥ ዳግም ተገለጠ። ይህ ታሪካዊ ጉዞ በመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ አዲስና ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋገረ። ለዘመናት የተጠነሰሰውና የትውልዶች ሕልም የነበረው ሀሳብ ሥጋ ይለብስ ዘንድ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተበሰረ።
የሕዝባችን የይቻላል መንፈስ ግዙፉን ፕሮጀክት በራሳችን አቅም፣ በራሳችን ጉልበትና በሙሉ ሕዝባዊ ተሳትፎ እውን ማድረግ ተቻለ።
በዓለም አቀፍ መድረኮችና በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ በጫና ለማንበርከክ የተነሱ፣ በውስጥና በውጭ ተግዳሮቶች የግድቡን ሥራ ለማስቀረት ቢሞክሩም የማይቻላቸውን ሞክረዋል፤ በመጨረሻም “ቪቫ ኢትዮጵያ!” የሚለው የአሸናፊነት መፈክር በዓለም አቀፍ መድረክ ለኢትዮጵያ አስተጋብቷል።
የተቋማት ዲፕሎማሲ፣ የመከላከያና የሳይበር ደህንነት ተቋማት ጽናት እንዲሁም የመላው ሕዝብ የጋራ ተሳትፎ የኢትዮጵያን አሸናፊነት አረጋገጡ።
ይህ የኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆምና ለልማት መተባበር፣ ለዘመናት ሲነገር የኖረውን “አባይ ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለውን የቁጭት አባባል አስቀርቶ ወንዙ ከተፈጥሯዊ ሀብትነቱ በተጨማሪ ለሀገራዊ ልማትና ብርሃን እጅ እንዲሰጥ አደረገ።
የህዳሴ ግድብ ትርጉም በኮንክሪቱ ግዙፍነትና በሜጋ ዋት መጠኑ ብቻ አይለካም። ከአራቱም አቅጣጫዎች የሚመጡ ገባር ወንዞች ተዋህደው አባይን እንደሚፈጥሩ ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያንም የተለያዩ አቅሞች፣ ልዩነቶችና እውቀቶች በአንድ ዓላማ ተደምረው ታላቅ ሀገራዊ ውጤት መፍጠር እንደሚችሉ ማሳያ በመሆኑ እንጂ።
የዓድዋ ታሪክና የህዳሴው ጉዞ አንድ ታላቅ እውነት አስተምረውናል፤ ታሪካዊ ድል በተከበረበትና በተከናወነበት ቦታ ብቻ ረክቶ መቆም አይበቃም፤ የቀድሞውን ድል ወደ አዲስ ሁለንተናዊ ውጤት መቀየር ያሻል እንጂ።
ይህ የአባይ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ ከመንግሥት ወደ መንግሥት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ የሥራ፣ የአንድነትና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ታላቅ ታሪክ ነው።
ከዓድዋ የተወረሰው የአንድነት መንፈስ በዕውቀት ተጠናከረ፤ በሥራ ተፈተነ፤ በላብ ወደ ተጨባጭ ውጤት ተቀየረ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የንጋት ኮከብ ትዕምርትና የመነሻ ምዕራፍ እንጂ የመቻል ፍጻሜ አለመሆኑን ከልብ መቀበል ያስፈልጋል።
ግድቡን ለአዳዲስ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ድሎች ወኔ መቀስቀሻ አድርጎ መውሰድ ታሪክ እንዳይጫነንና ለቀጣይ ከፍታ እንድንዘጋጅ ያደርገናል።
በሠራዊት ከበበው
Exit mobile version