አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም በጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 56 ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኞች በመትከል በዓለም ላይ አዲስ ታሪክ መጻፍ ችላለች፡፡
መርሐ ግብሩ የመሬት መጎሳቆል፣ የደንና ብዝሀ ህይወት መጨፍጨፍ እንዲሁም የውሀ አካላቶቻችን መድረቅና በደለል መሞላትን ጨምሮ እንደ ሀገር የገጠሙ በርካታ የዘላቂ ልማት ተግዳሮቶችን ለማስቀረት ታስቦ ነበር የተጀመረው፡፡
በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ 50 ቢሊየን ችግኞችን በማህበረሰብ ተሳትፎ ለመትከል ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ በስምንት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን 56 ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል በዓለም ላይ አዲስ ታሪክ ጸፋለች፡፡
አጠቃላይ ከተተከሉ ችግኞች ከ3 ቢሊየን በላይ የሚሆኑት በአንድ ጀምበር የተተከሉ መሆናቸውም በዓለም ላይ ታሪክ ሆኖ ተጽፏል፡፡
በመርሐ ግብሩ ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት የጥምር ደን ግብርና ማለትም ፍራፍሬ፣ ቡና፣ የመኖ ዝርያዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የደን ዛፎች ናቸው፡፡
ይህ ታላቅ የልማት ድል የተሳካው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር በተሰጠው ቁርጠኛ አመራርና መናበብ ነው፡፡
ይህ በመንግሥት መዋቅር የታየው የተናበበ አመራር በዓመት ከ25 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ማንቀሳቀስ አስችሏል፡፡
ችግኝ ከመትከል ባሻገር የደን ጭፍጨፋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፤ በዓመት ይጨፈጨፍ ከነበረው 92ሺህ ሄክታር ደን ወደ 27 ሺህ ሄክታር ማውረድ ተችሏል፡፡
በእርሻ ማሳ ያለ የአፈር ክለት በዓመት ከነበረው 130 ቶን ሄክታር ወደ 54 ቶን በሄክታር ቀንሷል፤ ወደ ውሀ አካላት የሚገባ የአፈር ደለል ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን ወደ 208 ሚሊየን ቶን በዓመት መቀነሱ ታውቋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ወደ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚጠጋ የስራ እድል ለወጣቶችና ለሴቶች መፍጠር፣ በበርካታ አካባቢዎች የፍራፌሬና የደን ክላስተር እየተፈጠረ የገበሬው የኢኮኖሚ ዋስትና እየሆነ መምጣቱ ከመርሐ ግብሩ ስኬቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
ወጣቱ ሀገሩን እንዲወድ፣ እንዲቆረቆርና እንዲተባበር ያደረገ ሲሆን፤ እንደ ሀገር ትላቅ የልማት መርሐ ግብር ቀርፀን መተግበር እንደምንችል ትልቅ ተሞክሮ የወሰድንበትና ለዓለምም ያሳየንበት ነው፡፡
በተለይ እንደ አየር ንብረት ለውጥና የበረሀማነት መስፋፋት ካሉ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች ጋር ተያይዞ ሀገራችን ሰለባ ብቻ ከመሆኑ የመፍትሄው አካል መሆኗን ለዓለም ያሳየችበት መርሐ ግብር ነው፡፡

