Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው እግዚአብሔር በቸርነቱ የሚሰጠን አዲስ ዓመት ጥላቻ እና ጥልን ትቶ በይቅርታ መንፈስ በአንድነት መቀጠል ይገባናል ብለዋል፡፡

ዜጎች ያለፈውን ዓመት በንጹህ ህሊና በጥልቀት በመገምገም ለተፈጸሙ ስህተቶች ይቅርታ በመጠየቅና ድጋሚ ላለመድገም መወሰን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አዲሱ ዓመት ለሁሉም የተሻለና ሰላማዊ እንዲሆን የእያንዳንዱ ዜጋ ንቁ ተሳትፎና እውነተኛ መታደስ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል፡፡

እግዚአብሔር ከታላቅ ቸርነቱ የተነሣ የመታደስ ዘመንን በየዓመቱ ከመስጠት አልተቆጠበም፤ እንደ ሁልጊዜ አሁንም አዲሱን ዘመን ባርኮ ሰጥቶናል፤ ሆኖም አዲሱ ዘመን የመጽናናት ዓመት እንዲሆንልን የእኛ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው መዘንጋት የለብንም ብለዋል፡፡

ለሁሉም መድኃኒቱ ቀና አእምሮ ነውና በአዲሱ ዓመት እግዚአብሔር ቅንና በጎ አሳቢ አእምሮ እንዲሰጠን በሱም ያሉብንን ጉድለቶች አርመንና አስተካክለን ሰላም የሰፈነበት የመጽናናት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

Exit mobile version