Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ተመራጭ የሆነችው አዳማ

 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዳማ ከተማ በዘመናዊ የከተማ ልማት ውበትና በተፈጥሮ በረከት ያጌጠች ንቁ የኢኮኖሚና የባሕል ማዕከል ናት።

ከተማዋ ካሏት በርካታ መገለጫዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰውና በፍጥነት እያደገ የመጣው የኮንፍረንስ ቱሪዝም ዘርፍ አንዱ ነው።

አዳማ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችን፣ ኤግዚቢሽኖችንና ሲምፖዚዬሞችን በብቃት በማስተናገድ ረገድ ትልቅ ሚና አላት፤ ይህንን ሚናዋን ከፍ ባለ መልኩ አጠናክራ እየሰራችበት ትገኛለች ፡፡

ከአዲስ አበባ ያላት ቅርበት፣ ፈጣን መንገድን ጨምሮ በዋና የመጓጓዣ መስመሮች ላይ መገኘቷ፣ እየተሻሻለ የመጣው የሆቴልና የስብሰባ አዳራሽ አቅም ከተማዋን ለጉባዔዎች፣ ለሴሚናሮች፣ ለዎርክሾፖችና ለተለያዩ ሙያዊ ዝግጅቶች ምቹ መዳረሻ አድርጓታል።

ከተማዋ የእውቀትና የምርምር ማዕከል የሆነውን የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የትምህርትና ምርምር ተቋማትን መገኛ መሆኗ ለሳይንሳዊ፣ ለሙያዊና ለእውቀት ልውውጥ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

የኮንፍረንስ ቱሪዝም የጉባዔ ተሳታፊዎች ሆቴል፣ ምግብ፣ ትራንስፖርት፣ መዝናኛና ሌሎች አገልግሎቶችን ሲጠቀሙ የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃሉ፤ በዚህም ለአካባቢው ነጋዴዎችና ለወጣቶች የገቢና የሥራ ዕድል ይፈጠራል።

በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጉባዔዎችን በማስተናገድ ያላትን ልምድና አቅም ማጠናከሯም አዳማን የስብሰባ፣ የእውቀት ልውውጥና የንግድ ትስስር ማዕከል የማድረግ ሒደቱን ያፋጥናል።

በመሆኑም አዳማ ተደራሽነቷን፣ የመስተንግዶ አቅሟን፣ የእውቀት ማዕከልነቷንና የቱሪዝም ሀብቷን በማጣመር ኮንፍረንስ ቱሪዝምን ከተጨማሪ የቱሪዝም አይነት ባለፈ አዲስ የከተማ እድገት አቅም እያደረገችው ነው።

በአመለወርቅ ደምሰው

Exit mobile version