Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የነዳጅና ፔትሮሊየም ኢኒስቲትዩት ተማሪዎችን ሊቀበል ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ስር ለተቋቋመው የነዳጅና ፔትሮሊየም ኢኒስቲትዩት በ22 ልዩ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ሊቀበል ነው፡፡
ኢኒስቲትዩቱ በካሉብ፣ ሂላላና ጎዴ ከተሞች በ10 ቢሊየን ዶላር እየተከናወኑ ያሉትን የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያና የኤል ኤን ጂ ማዳበሪያ ፋብሪካ ጎዙፍ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የፔትሮሊየምና ኢነርጂ ዘርፍ ለመደገፍ የተመሰረተ ነው።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው በ2019 የትምህርት ዘመን ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎች ባስተላለፈው መልዕክት፤ የነገ የኢነርጂ ዘርፍ መሪዎችን ለማፍራት የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ነዳጅና ፔትሮሊየም ኢኒስቲትዩት እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢኒስቲትዩቱ በኢነርጂው ዘርፍ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለሚፈጥሩ ሙያዎች የሚያስፈልጉትን ቴክኒካዊ ክህሎቶች ለማስታጠቅ የተዘጋጁ ልዩ የዲግሪ ፕሮግራሞችን ማቅረቡንም ዩኒቨርሲቲው ገልጿል፡፡
በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ኢንጂነሪንግና በዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ጂኦሎጂ ኢንጂነሪንግ እንዲሁም በሪዘርቫየር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ሥር በሚገኙ በርካታ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎችን ይቀበላል፡፡
በፔትሮኬሚካል ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ፣ የነዳጅና የጋዝ ማጣሪያ ማቀነባበሪያ እና የማዳበሪያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፎችም ይገኙበታል፡፡
በጤና፣ ደህንነትና ኢንቫይሮሜንታል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የዘላቂና ታዳሽ ሀይል እንዲሁም የፀሐይ ሀይል ኢንጂነሪንግ የትምህርት አይነቶችን እንደሚሰጥም ተመላክቷል፡፡
ትምህርቶቹ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት የተደገፉና በበይነመረብ በተሳሰሩ ስማርት የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ የሚሰጡ ሲሆን፤ ጥልቅ ምርምር ለማድረግ የሚያግዝ የላቀ ቤተ መጻሕፍትን ያካተተ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በኢንዱስትሪ ደረጃ የተዘጋጁ ሲሙሌተሮችና ዲጂታል መንትያ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት የዲጂታል ዳታ ሴንተር መዘጋጀቱንም ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡
Exit mobile version