Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተሳለጠ ሎጂስቲክስ ግዙፍ ኢኮኖሚና ብዙ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና አለው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመኑን የዋጀ ሎጂስቲክስ ግዙፍ ኢኮኖሚ እና ብዙ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ይጫወታል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ ሎጂስቲክስ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ሎጂስቲክስ የባሕር በር ፣ ትራንስፖርትን፣ የአየር መዳረሻን፣ የባቡር መስመርንና የወደብ አገልግሎትን የሚያጠቃልል መሆኑን ጠቁመው ÷ የወጭ እና ገቢ እቃዎችን ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ እንዲሁም ከፍተኛ ሕዝብ እና ግዙፍ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገራት ሎጂስቲክስ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ የኢትዮጵያን አንድ አስረኛ የሎጂስቲክ አገልግሎት የሚሸፍን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ለምታስገባቸው እቃዎች መነሻና መዳረሻ ሆኖ ማገልገሉን አንስተዋል፡፡

የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል የኮንቴይነር የመያዝ አቅም ከ500 ሺህ ወደ 1 ሚሊየን ማደግ መቻሉን ጠቅሰው ÷ ይህም የወጭ እና ገቢ እቃዎችን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

የሎጂስቲክስ አገልግሎት ችግር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ማነቆ ሆኖ መቆየቱን በማንሳት፣ የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል እነዚህን ችግሮች እንደሚፈታ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት የአፍሪካ መዳረሻ ማዕከል ለመሆን የጀመረችው ሥራ የተሟላ እንዲሆን የሞጆ እንዲሁም ሌሎች የደረቅ ወደቦች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

ዘመኑን የዋጀና የተሳለጠ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ይበልጥ እንደሚያጠናክርም አመልክተዋል፡፡

በትዕግስት ግዛቸው

Exit mobile version