Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከድሮን ትዕይንትነት ባሻገር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የአዲስ አበባ ሰማይ በአስደናቂ የድሮን እና የርችት ትዕይንት ደምቆ አድሯል።

በመዲናዋ በተካሄደው ልዩ የአዲስ ዓመት አቀባበል 3 ሺህ ድሮኖች ሰማዩን በኅብረ ቀለም በማስጌጥ የሀገሪቱን ታሪክ፣ ልማት እና የተስፋ መንገድ የሚያሳይ በአየር ላይ የተሳለ ምስል በድንቅ ቅንጅት አስመልክተዋል።

ይህ በአፍሪካ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ የድሮን ትዕይንቶች መካከል የሆነው ትዕይንቱ ከዘመን መለወጫ ዋዜማ ማድመቂያነት ባለፈ አንድምታው ብዙ ነው።

ትዕይንቱ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ዘርፍ እያሳየች ያለችውን ፈጣን ዕድገት የሚያበስር ትልቅ ማሳያ ሆኖ ያለፈ ሲሆን ድሮኖቹ በአየር ላይ በመብረር የተለያዩ ሀገራዊ መልዕክቶችን በደመቀ ሁኔታ ስለው አሳይተዋል።

እንዲህ ዓይነቱ ዘመናዊ የአቪዬሽን ልህቀትና ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አቀባበል ባህል ጋር መዋሐዱ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የብልጽግና እና የሉዓላዊነት ጉዞ ላይ መሆኗን የሚያመለክት ነው።

ትዕይንቱ የሀገር ውስጥ ተመልካቾችን ልብ ከመማረኩ ባሻገር በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሆኖ አልፏል።

የዚህ ዓመት የዘመን መለወጫ ዋዜማ የድሮን ትዕይንት በታሪክ ማኅደር ውስጥ በጉልህ የሚመዘገብ አዲስ አህጉራዊ ምዕራፍ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት በሲቪል እና ዲጂታል ቴክኖሎጂ መስክ በአፍሪካ ጠንካራ አቅም እና ተስፋ እንዳላት ለዓለም ያበሰረችበት ታሪካዊ ክስተት ነው።

በአብረሃም አበራ

Exit mobile version