አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቶ የሚቆጠሩ ታራሚዎች በምህረት የተፈቱት የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት በፍቅር፣ በይቅርታ እና በሰላም ለመጀመር ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2019 አዲስ ዓመትን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ ሀገራዊ ምክክራችን ገደ መልካም መሆኑን በምክክሩ ብቻ ሳይሆን በውጤቱም እያሳየ ነው ብለዋል።
በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶ የሚቆጠሩ ታራሚዎች መንግሥት በምሕረት እንዲፈቱ አድርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይሄንን ያደረገበት ዓላማ የሀገራዊ ምክክሩን ውጤት በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም ለመጀመር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ወደ ሀገራዊ ምክክር የመጡ ልዩ ልዩ ወገኖች በአንድም በሌላም ስሕተት የታሠሩ ወገኖች በይቅርታ እና በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ጠይቀው እንደነበር አስታውሰው፣ መንግሥት ጥያቄውን ተቀብሎ በሂደቱ የተስማሙትን መፍታቱን ገልፀዋል፡፡
የምክክሩም ዓላማ ኢትዮጵያውያን እንዲነጋገሩ እና የተግባቡባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች እንዲያቀርቡ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥትም ለምክክሩ ሐሳቦች ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ የይቅርታ ሂደት ማሳየት መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህ የይቅርታ ሂደት የተፈቱ ወገኖች በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚታመን እንዲሁም ካለፈው መንገድ በመማር የወደፊቱን መንገድ የሰላምና የዴሞክራሲ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡም እነዚህ ወገኖች በሀገር ሰላምና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ማገዝና መምከር እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መነጋገር፣ መከራከርና መፎካከር ሲቻል ግጭትና ጦርነት አዋጪ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የብዕርና የሐሳብ ጊዜ እንጂ የጠመንጃ እና የጉልበት ጊዜ ማለፉን በመግለጽ የኢትዮጵያ የዘመን መጽሐፍ ካሁን በኋላ የጠመንጃና የጉልበት ታሪክን አይመዘግብም ብለዋል።
በቀጣይም የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ የተለያዩ ዕሳቤዎችንና አካሄዶችን በብሔራዊ ጥቅም አስተሣሥረን የምንጓዝበት ዓመት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

