አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር እውነተኛ አቅም የሚለካው በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ በሚታለም ህልም ሳይሆን፤ በፈተናዎች መካከል ተስፋን ሰንቆ የዕድል መንገዶችን በመጥረግ በሚደረግ የጽናት ጉዞ ነው።
የታሪክና የጽናት ምድር የሆነችው ኢትዮጵያም በተደራራቢ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፈተናዎች ማዕበል ውስጥ አልፋ፤ የመዋቅራዊና የዘርፍ ማሻሻያዎችን መሠረት በመጣል የዕድገት መንገዷን በአዲስ መንፈስ እያደሰች ትገኛለች።
ይህ የትራንስፎርሜሽን ጉዞ የአንድ ዘርፍ ጊዜያዊ ስኬት ሳይሆን፤ በግብርና፣ በማዕድን፣ በኃይል፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና በግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ የሚታይ ሁለገብ እና ሰፊ የለውጥ ጉዞ ነው።
እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2024 ጀምሮ ያስጀመረቻቸው ሁለገብ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዘርፈ ብዙ ውጤት በማምጣት የፋይናንስ ዘርፉን ያጠናከሩ ናቸው።
እነዚህ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቅረፍ የወጪ ንግድን ማደራጀት መቻላቸውንም ተቋማቱ በመረጃቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመንግሥትን የሀገር ውስጥ ገቢ የማሰባሰብ አቅም ማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አፈጻጸምን ማሻሻል፣ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያዎችን ማሳደግና የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት አቅምን ማጠናከር ላይ አዎንታዊ ውጤቶች እየታዩ ነው።
ከማክሮ ኢኮኖሚው ጎን ለጎን፣ በትራንስፖርትና በኃይል ማመንጨት ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያዎች እና የታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንቶች ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ዕድገት ጠንካራ መሠረት እየጣሉ ነው።
በተመሳሳይ የዲጂታል ሽግግሩ ኢኮኖሚውን ከባህላዊ አሠራር ወደ ቴክኖሎጂ ተኮር አሰራር እያሸጋገረ ይገኛል።
በዚህም የዲጂታል ኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የኢንዱስትሪ ማምረትን፣ የማዕድን ቁፋሮንና የግብርና ምርታማነትን እንደ ቀዳሚ የልማት ዘርፎች በማስቀመጥ አዳዲስ አቅሞችን ፈጥሯል።
ይሁንና ይህን የተገኘ አዎንታዊ የዕድገት እንቅስቃሴ ወደ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለመቀየር ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ፣ የምርታማነት ማደግና የዜጎች የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ወሳኝ ይሆናሉ።

