አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀረጹት ዘርፎች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው አሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ፡፡
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ፥ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከተመዘገበባቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ናት ብለዋል።
ይህም በሀገሪቱ ከተተገበሩት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ከተከተለችው የረጅም ጊዜ የልማት ስትራቴጂ የሚመነጭ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተተገበረባቸው ዘርፎች ማለትም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተመዘገቡት ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን አመልክተዋል።
በተለይም በማዕድን ዘርፍ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከወርቅ የወጪ ንግድ ብቻ 5.7 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ታሪካዊ ገቢ መመዝገቡን ጠቅሰው የ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ዕድገት እንዲመጣ ማስቻሉን አብራርተዋል።
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በግብርናውም ዘርፍ ከባህላዊ ወደ ሜካናይዝድ አሰራር በመሸጋገር ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም፣ በአገልግሎት ዘርፎች የተመዘገቡት እነዚህ ስትራቴጂካዊ ስኬቶች የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ፈጣን እና ዘላቂ እያደረጉት መሆኑን ተናግረዋል።
በፋይናንስ ዘርፉም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎች የግል ባንኮች ያስመዘገቡት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የትርፍ መጠን በሀገሪቱ የጎላ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላትን መሰረት በማጠናከር ረገድ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማትና የጋዝ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውና መጠናቀቃቸው ለኢኮኖሚው ከፍተኛ እንቅስቃሴ መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ከአምስት ሺህ ሜጋዋት ወደ 10 ሺህ ሜጋዋት ገደማ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የግል ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ አልፈው በውጭ ሀገራት ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ አቅሙን አጠናክሮ በመቀጠል በክልሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ የሚያደርጉ ግዙፍ ኩባንያዎችን መፍጠር እንደሚገባው አሳስበዋል።

