አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት መሪነት በጀመረችው የዲፕሎማሲ ከፍታ ጉዞዋ ከቀጣናውና ከአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ባሻገር ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን እያጎላች ቀጥላለች፡፡
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፤ ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት ያላትን ሚና በተመለከተ በአድናቆት የመሰከሩትም ይህንኑ እውነት ነው፡፡
የሕንዷ ኒው ዴልሂ 18ኛውን የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን እያስተናገደች ትገኛለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸው በዚህ ታላቅ ሁነት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግን ጨምሮ የአባል ሀገራቱ መሪዎችም ለዚሁ ጉባኤ በሕንዷ ኒው ዴልሂ ከትመዋል፡፡
ከጉባኤው መጀመር አስቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአባል ሀገራቱ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሕንዱ አቻቸው ናሬንድራ ሞዲ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የሁለቱን ሀገራት አጋርነትን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ሀሳብ መለዋወጣቸውን አመልክተዋል።
ውይይታችን የመከላከያ ትብብርን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ፣ የማዕድን ልማትና ወደ ኮፕ 32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ያለንን አጋርነት ማጠናከር በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።
እነዚህ መስኮች በተግባር የታገዘ ትብብርን ይበልጥ ለማሳደግና ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን የደቡባዊ ዓለም ሀገራትን ተሰሚነት ለማጉላት ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሁለቱን መሪዎች ውይይት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ከሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅሞች ጋር በተገናኙ ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል ብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ለምታደርገው ተሳትፎ አድናቆታቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መገኘት የደቡባዊ ዓለም ሀገራትን የጋራ ድምጽና ተደማጭነታቸውን ከፍ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል፡፡
ይህ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምስክርነት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምጽ ከመሆን ተሻግራ ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሸፍነውን የደቡባዊ ዓለም ሀገራትን (Global South) ተደማጭነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኗን ያመላከተ ነው፡፡
ከዚህም ባለፈ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከተሳትፎ ባሻገር በጎ ሚና ስትወጣ መቆየቷ፤ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተፈላጊነቷ እያደገ ለመምጣቱ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

