Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በማሌዢያ ኤምባሲዋን እንድትከፍት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በማሌዢያ ኤምባሲዋን እንድትከፍት የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር ውይይት አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም፣ ኢትዮጵያ በማሌዢያ ኤምባሲዋን እንድትከፍት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሌዢያ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ በአዲስ አበባ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ከ43 ዓመታት መቋረጥ በኋላ ዳግም መክፈቷን በውይይቱ ወቅት አስታውሰዋል።

ይህ ታሪካዊ ርምጃ በሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንና በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች ሁለገብ ትብብርን ለማጠናከር የተግባር አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ማሌዢያ ከብሪክስ ጋር ለምታደርገው ተሳትፎ ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በውይይቱ በሁለቱ ሃገሮች መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመለወጥ ቀጣዩን የመጀመሪያ የሁለትዮሽ ምክክር ለማካሄድ ከስምምነት ተደርሷል።

Exit mobile version