አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በየዓመቱ የዘመን መለወጫን ስናከብር አብዛኛውን ጊዜ ትኩረታችን ያሳለፍነውን ዓመት በሰላም ሸኝቶ አዲሱን ዓመት በደስታ በመቀበል የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን በቀን መቁጠሪያዎች ለውጥ ውስጥ ማስተናገድ ላይ የተወሰነ ነው።
ሆኖም አሁን የምንገኝበት ወቅት ከወትሮው የተለየና ከዓመት ወደ ዓመት ከተደረገ ተራ የጊዜ ሽግግር እጅግ የላቀ ጥልቅ ታሪካዊ ትርጉም ያለው ነው።
ይህ ዘመን የዕለት ተዕለት የቀን መቁጠሪያ ገጽ የሚገለጥበት ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተጫናት የፈተና አዙሪት ወጥታ ወደ ዘላቂ ልማትና ብልፅግና ለማምራት እያንሠራራች ያለችበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶች የሕዝባችንን ተስፋ ሲፈታተኑ፣ ሀገራዊ ጉዟችንንም ወደ ሕልውና አደጋ ሲጎትቱት ቆይተዋል። ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት በመደመር መንግሥት እሳቤ የተከናወነው ሀገራዊ ሪፎርምና የልማት አቅጣጫ ጉዞ ይህንን ሙሉ በሙሉ የቀየረ ሆኗል።
ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተመዘገቡት ስኬቶች የኢትዮጵያን የእድገት አዙሪት ከቁልቁለት ወደ ከፍታ ያሸጋገሩ ናቸው።
ትናንት ሲያሰናክሉ የቆዩ ድካሞችና ተስፋ አስቆራጭ ሁነቶች ዛሬ ቦታቸውን ለጽኑ የማንሠራራት መሰረቶች ለቀዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ እና በታላላቅ መሰረተ ልማቶች ላይ የተገኙ ስኬቶች ሀገራችን እራሷን ችላ እንድትቆም የሚያስችላትን አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። ዛሬ ቆመን የምንመለከተው የትናንቱን ውድቀት ሳይሆን፣ የነገዋን ባለ ብሩህ ተስፋ ኢትዮጵያን እውን የሚያደርገውን የማንሠራራት ጉዞ ነው።
ቀድሞ በመዝገበ ቃላት ለችግርና ለረሃብ ፍቺ እንደ ምሳሌነት ትቀርብ የነበረችው ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ላይ ባስመዘገበችው እመርታ በስንዴ ምርት ከራስ አልፎ ለአህጉሪቱ ማዕድ የመድረስ አቅምን ተጎናፅፋለች።
በእርዳታና ብድር ላይ ጥገኛ የነበረው ኢኮኖሚዋ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ገንብቶ ከማጠናቀቅ ባለፈ ከአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ በርካታ ታላቅ ትልሞችን የምታሳካበትን መሰረት ጥላለች።
አዲሱ ዓመትበኢትዮጵያውያን መካከል የልዩነት ግንቦችን ገንብተው ሲያነታርኩ፣ ሲያጋጩና ሲያገዳድሉ የነበሩ መሰናክሎችን በማፍረስ ወንድማማቾችን ለአንድ ሀገር በአንድነት ለማቆም የመከሩበት ሀገራዊ ምክክር በተደረገ ማግስት የመጣ ባለ አዲስ ተስፋ ዓመትም ነው።
ሕዝቡም ያሳለፈውን መከራና የገጠመውን ፈተና ወደ አሸናፊነት መንፈስ በመቀየር፣ አሁን በተጣለው መሠረት ላይ የነገዋን የበለፀገች ሀገር መገንባት እንደሚችል በሙሉ እምነት በመታተር ላይ እይገኛል።
አዲስ ዘመን፣ አዳዲስ ሀገራዊ ግቦች እና ለከፍታ የሚደረግ የጉዞ ምዕራፍ ይዞ መጥተል።ይህ አዲስ ወቅት አዲስ መንግሥት የሚመሰረትበት፣ የተወጠኑ ትልሞች ለስኬት የሚበቁበትና ወደ እድገትና ብልፅግና መሪ የሆኑ አዳዲስ ሀገራዊ ግቦች የሚቀመጡበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለላቀ ውጤትና ለተሻለ ስኬት ራሱን የሚያዘጋጅበት፣ ሀገራችን ሙሉ በሙሉ ወደ ማንሠራራትና የከፍታ ዘመን የምትሸጋገርበት ታሪካዊ ዘመን ነው።
ወደፊት የሚከናወኑ ሀገራዊ ተግባራትና ዕቅዶች ሁሉ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የእርዳታ ጥገኝነትና የማሽቆልቆል አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወጥታ፣ በአህጉረ አፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪና በራሷ የምትተማመን ሀገር እንድትሆን የሚያስችሉ ናቸው።
ይህ አዲስ ምዕራፍ የተቃጣብንን ፈተናዎች አሸንፈን የከፍታችንን ማማ የምንጨብጥበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
አዲሱ ዘመን የተስፋ ብቻ ሳይሆን የጠንካራ ሥራና የተግባር ዘመን ነው። እያንዳንዳችን በየተሰማራንበት ዘርፍ ለሀገራችን ማንሠራራት አስተዋጽኦ ስናደርግ፣ የቀድሞ ታሪካችንን ሙሉ በሙሉ በመቀየር ለቀጣዩ ትውልድ የበለፀገችና የተከበረች ኢትዮጵያን እናስረክባለን።
ይህ ወቅት የጋራ ሕልማችንን እውን ለማድረግ ሁላችንም የምንነሳበትና ለላቀ ውጤት የምንሰለፍበት ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ነው።
በመሆኑም ይህ ዘመን ተራ የዓመት መለወጫ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ አቅጣጫችን የተለወጠበትና ወደ ባለ ተስፋዋ ኢትዮጵያ የሚወስደውን በር የከፈትንበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
በመልካም ፈቃዱ

