Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ፡ ብሪክስ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያሳየች ያለው ስኬታማ ዲፕሎማሲ በተለያዩ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን የበቃችው እንዲሁ በቀላሉ እና በሚመች መንገድ ሳይሆን በብዙ የዲፕሎማሲ ጥረት እና ንግግር ነው፡፡
ይህ አባልነት ኢትዮጵያን በብዙ ዘርፉ የሚጠቅማት እና በዓለም መድረክ ያላትን ተሳትፎ ብሎም የድምጿን ክብደት የሚያገዝፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ከዓለም ታላላቅ መንግሥታት ከሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ከሌሎች 11 የዓለም ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች፡፡
ይህ ስብስብ የዓለማችንን 45 ከመቶ በላይ የሕዝብ ብዛት እና የዓለምን 35 ከመቶ የሚሆነውን ጠቅላላ የውስጥ ምርት የሚሸፍን ግዙፍ ጥምረት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ታዲያ ይህን ስብስብ ተቀላቅላ የዲፕሎማሲ አቅሟን አሳድጋለች፡፡ የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጅ በነጻነት የምትገበያይበትን እድል የከፈተና የዓለም የኢንቨስተሮች ዓይን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሆን ያስቻለ ነው፡፡
ይህ የዲፕሎማሲ ከፍታ ኢትዮጵያ በሌሎችም ዘርፎች የጀመረችውን እድገት እንድታስቀጥል እና እየጠየቀች የምትገኘውን የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ በድል እንድትወጣ ሚናው ጉልህ ነው፡፡
የዘንድሮው 18ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይም የመደመር መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የታዩ ለውጦችን ለጉባዔው አቅርበዋል፡፡
‎በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን፤ አሁን ያለው መልካም ዕድል እነዚህን አቅሞች በማስተሳሰር የላቀ እሴት መፍጠር እና ይህ እሴት ደግሞ ሀብቱ በሚገኝበት ቦታ መመረት እንዲችል ማድረግ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማዕድን ልማት፣ በታዳሽ ኃይል እና እያደገ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መሠረቷ ላይ እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ ናት ነው ያሉት።
‎የብሪክስ መድረክ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ብሪክስ የአባል ሀገራቱ አቅም ድምር ውጤት በመሆኑ ቀጣይ ኢትዮጵያ ምን ልታበረክት ትችላለች የሚለው በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ የጀመረችውን የዲፕሎማሲ ስኬት ይበልጥ ለማሳደግ የምታከናውነውን ዘርፈ ብዙ ተግባር አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
በእመቤት ሲሳይ
Exit mobile version