Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በብሪክስ፡ ከአባልነት ወደ ዕድል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነት የምታገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም አጠናክራ ለማስቀጠል ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች፡፡
የብሪክስ ጉባዔ ኢትዮጵያ ስለራሷ ጉዳይ በራሷ አንደበት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድትናገር ከማስቻሉም በላይ በርካታ እድሎችን የሚያመጣ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ዲፕሎማሲያዊ ተሳትፎን ከማጠናከር ባለፈ ለኢኮኖሚ፣ ለንግድ እና ለኢንቨስትመንት አዳዲስ እድሎችን ይከፍታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ መሳተፏ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ከማጠናከር ባሻገር፣ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ለማስፋት ዕድል ይፈጥራል።
ከጉባዔው ጎን ለጎን የሚደረጉ ውይይቶች በንግድ፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንትና በልማት ዙሪያ የትብብር እድሎችን ለመፍጠር ያግዛሉ።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት በማስፋት የውጭ ገበያ ተደራሽነቷን ለማሳደግ እድል አግኝታለች።
በተለይም በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እየተፈጠሩ ነው።
ከብሪክስ ጋር የተያያዙ የልማት ፋይናንስ ተቋማት እና የአባል ሀገራት የፋይናንስ አቅም ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የፋይናንስ አማራጭ የሚሆኑ ናቸው። ይህም የመንገድ፣ የኃይል፣ የውሃ እና የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን ጉልህ ሚና አለው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ አፍሪካ የበርካታ ማዕድናት ሀብት ባለቤት መኗንና የብሪክስ አባል ሀገራት ደግሞ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የገበያ አማራጭ እንዳላቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በማዕድናት፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና እያደገ ያለውን የኢንዱስትሪ አቅሟን መሰረት ባደረገ መልኩ አጋርነቶችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ዘርፈ ብዙ ሃብት አቀናጅቶ ለመጠቀምና በጥሬ ሃብቱ ላይ እሴት ለመጨመር የብሪክስ ጥምረት ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡
ብሪክስ ኢትዮጵያ የራሷን የልማት ፍላጎትና የአፍሪካን ጥቅም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ ለማሳየት ተጨማሪ መድረክ ይሰጣታል። በዚህ መድረክ ላይ መሳተፍ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አማራጮች ከማስፋት ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ መድረክ የምታገኛቸውን የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ እድሎች ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት የመቀየር የቤት ሥራዋን እየተወጣች ነው፤በቀጣይም አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት የክብር ማዕረግ ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ እድልን ወደ እውነተኛ ልማት ለመቀየር የሚያገለግል ስትራቴጂያዊ ጥምረት መሆኑን በመገንዘብ በቁርጠኝነት መስራትና ትሩፋቱን ማጠናከር ይገባል፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version