አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን የሚያደርጉ ኩባንያዎችን ቁጥር ማሳደግ ተችሏል አለ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር።
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ተወካይና ቡድን መሪ ካሳ አላምራው ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፣ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጠንካራ መዋቅራዊ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።
በዚህም በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት በ2018 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 96 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደተቻለ ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የዘርፉ ድርሻ ከጠቅላላ ሀገር ውስጥ ምርት እድገት በ2010 በጀት ዓመት ከነበረበት 6 ነጥብ 2 በመቶ በ2018 ዓ.ም ወደ 6 ነጥብ 82 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪው አማካኝ ዕድገትም በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ከ5 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 12 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ብሏል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ከ51 በመቶ ወደ 69 ነጥብ 3 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የኤክስፖርት ገቢም በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 308 ሚሊየን ዶላር በ2018 በጀት ዓመት ወደ 607 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ማደጉን አስረድተዋል።
እንዲሁም በአዲስ መልክ በተተገበረው አቀራረብ የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ ከ30 በመቶ ወደ 46 ነጥብ 41 በመቶ ከፍ ማለቱ አብራርተዋል።
የሃገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አዲስ ኢንቨስትመንት ያደረጉ ኩባንያዎች ቁጥር ከ112 ወደ 165 መድረሱን ነው የገለጹት፡፡
የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ብዛት ከ2 ሺህ 760 ወደ 4 ሺህ 233 ያደገ ሲሆን፤ ይህም በዘርፉ የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል ከ45 ሺህ 550 ወደ 448 ሺህ 717 ከፍ እንዲል አድርጓል ነው ያሉት።
ለእነዚህ ስኬቶች መመዝገብ እንደ ሀገር ለዘርፉ የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፣ የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ የተተገበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች፣ አዳዲስ ስትራቴጂዎችና የህግ ማዕቀፎች በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

