አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ዲፕሎማሲያዊ መድረክ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል፡፡
በተለይም ለአስርት ዓመታት ስታካሂድ ለቆየችው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ከስብስቡ ትልቅ የፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አግኝታለች።
በሕንድ ኒውዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸውን ቻይና፣ ሕንድ እና ሩሲያን ጨምሮ አባል ሀገራቱ፤ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን የመቀላቀል ሂደት በሙሉ ድምፅ ደግፈዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ተደማጭነትና የመደራደር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል፤ ሀገሪቱ ለዓመታት የተጓዘችበትን ረጅም የድርድር መንገድ የሚያሳጥርና የሚያፋጥን ነው፡፡
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ከነባር የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ሀገራት ጋር ለምታደርጋቸው የሁለትዮሽ የገበያ ዕድልና የታሪፍ ድርድር የትብብር ድልድይ ፈጥሮላታል።
የብሪክስ አባል ሀገራት የኢትዮጵያን የንግድ ህጎች፣ የታሪፍ አሠራሮችና የፋይናንስ ሥርዓቶች ከዓለም አቀፍ አሰራር ጋር ለማጣጣም የሚያስችሉ የልምድ ልውውጦችንና የቴክኒክ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ይህ ተቋማዊ አቅምን የማጠናከር ሥራ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት ደንቦችንና የንግድ ውሎችን በብቃት እንድታሟላ የሚረዳ ሲሆን፤ በሀገር ውስጥ የሚደረጉ የኢኮኖሚና የንግድ ማሻሻያዎች በስኬት እንዲተገበሩም ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።
የብሪክስ አባልነት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመጨመርና የወጪ ንግድ ምርቶች የገበያ ዕድልን በማስፋፋት የሀገር ውስጥ አምራቾችንና የንግድ ዘርፎችን ተወዳዳሪነት እያሳደገ ይገኛል፡፡
በዚህም የኢኮኖሚ አቅሟ ይበልጥ ያድጋል፤ ከዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የውድድር ተፅዕኖዎችን የመቋቋም አቅሟም ይጎለብታል።
የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጉዞ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ትናንትና ከትናንት በስቲያ በሕንድ ኒው ዴልሂ የተካሄደው 18ኛው የስብስቡ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የድርጅቱ አባልነት ጉዳይ አባል ሀገራቱ የሰጡት ድጋፍ ይህን ያረጋገጠ ሆኗል፡፡
በአብረሃም አበራ

