አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር የፖለቲካ ብስለትና የኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚለካው በጊዜያዊ የስልጣን ሽግግሮች ወይም በግለሰቦች ላይ በተወሰነ የአመራር ብስለት ብቻ ሳይሆን፤ በዘመናት መካከል ጸንተው በሚቆሙ ሀገራዊ ተቋማት ጥንካሬ ነው።
የሀገራት ታላቅነት ምስጢር መሰረቱን የሚጥለው የህግ የበላይነትን እና የህዝብን ድምጽ የሚያስከብሩ ተቋማትን በመገንባት ነው፡፡
ግለሰቦች የተፈጥሮን ህግ ተከትለው ይመጣሉ፣ ይሄዳሉም፤ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋም ግን ትውልድን ተሻግሮ የሀገረ መንግሥትን ህልውና ያስቀጥላል።
ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ውስብስብ የፖለቲካ ምህዳር ወደ ተረጋጋ የዴሞክራሲ መስመር ለመቀየር በተደረገው ጥረት፤ ሶስት ዋና ዋና ተቋማት የሀገረ መንግሥታችን የጀርባ አጥንት ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ ሲሆን፤ ህዝቡ ያለ ምንም ተፅዕኖ በነጻነት የመረጠበትና የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነቱን ያረጋገጠበት ተቋም ነው።
ገለልተኛ የምርጫ ተቋም መኖሩ የመራጩን ህዝብ እምነት ከመገንባቱም በላይ፤ የምርጫ ውጤቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲቀበሉ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ሌላው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው፤ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ ስኬታማና ታሪካዊ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተካሂዷል።
ይህ ሂደትም ለዘመናት የቆዩ መሰረታዊ የፖለቲካና የማህበራዊ ልዩነቶችን በንግግርና በምክክር በመፍታት የጣለው መሰረት፤ ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ነው::
የህዝብ ድምጽና ፍላጎት በቀጥታ የሚንጸባረቅበት፣ ሀገራዊ ህጎችና ፖሊሲዎች የሚፈልቁበት የተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ወሳኝ መሰረትን ይጥላል፡፡
የምክር ቤቱ መጠናከር የመንግሥትን አሰራር ለመቆጣጠርና የህዝብ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ መሰረት ሆኗል።
አሸናፊ ፓርቲዎች በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በኩል መንግሥት የሚመሰርቱበት ዴሞክራሲያዊ ሂደት፤ የሀገረ መንግሥቱን ጉዞ የሚያሳልጥና የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ነው።
ተቋማት ሲጠነክሩ የፖለቲካ ሂደቶች ግልጽ፣ ታማኝ እና ሰላማዊ ይሆናሉ።
አሁን በመከናወን ላይ ያለው የተቋማት ማጠናከር ስራ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ለኢኮኖሚ እድገት እና ብልጽግና ብሎም ለትውልድ ተስፋ የሚሆን አስተማማኝ መሰረት የሚጥል ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በመልካም ፈቃዱ

