አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥንታዊ ስልጣኔ እና ባህል ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያ እና ኢራን፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ ከ75 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡
የአክሱም ሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እና የፐርሺያ ሥልጣኔ ማዕከሏ ኢራን፤ በተለይም በንግድና ኢኮኖሚ መስኮች ለዓመታት ጠንካራ ትብብር መፍጠር ችለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በሕንድ ኒው ዴልሂ ከተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢራን ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን ጋር መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቀይ ባሕር አካባቢ ባሉ ወቅታዊ ሁነቶችና አጠቃላይ የቀጣናው የደኅንነት ሁኔታ የውይይታቸው ዋና ጉዳይ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የውይይትን አስፈላጊነትና የቀጣናውን መረጋጋት እውን ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረናል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በሸፍጥ የባህር በር እንድትነጠቅ መደረጉ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ያላትን የላቀ አስተዋጽኦ በሰፊው የቀይ ባህር አካባቢ ለማጠናከር የምትችልበትን እድል ገድቦ ቆይቷል፡፡
የቀይ ባህር ቀጣና በዓለም ቁልፍ የንግድ መተላለፊያ እንደመሆኑ መጠን፤ የቀጣናው ሰላምና ደሀንነት መጠበቅ ከአካባቢው ሀገራት ባሻገር በተቀረውም ዓለም ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡
ለዚህም ነው ከቀይ ባህር 60 ኪሎ ሜትሮች ገደማ ብቻ ርቃ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ የተነጠቀችውን ታሪካዊ የባህር በር ባለቤትነት የሕልውናዋ ጉዳይ አድርጋ እየተንቀሳቀሰች የምትገኘው፡፡
ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው የቀይ ባህር ቀጣናን ጉዳይ በትኩረት ማንሳታቸውም፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው የደህንነት አጀንዳ ውጪ መሆን እንደማትችልና አስፈላጊ መሆኗን የሚያመላክት ነው፡፡
የመደመር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን ያስቀደመና የሚዛናዊ አቋም መርህን የተከተለ ነው፡፡
ከምዕራባውያንም ሆነ ከብሪክስ አባል ሀገራት፤ ከአፍሪካ አጋሮቿም ሆነ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር የምትፈጥረው ትብብርም በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
የሁለቱ መሪዎች ውይይትም፤ ኢትዮጵያ በየትኛውም የጂኦፖለቲካ ጎራ ሳትታጠር ብሔራዊ ጥቅሟን ባስቀደመ ሁኔታ ሚዛናዊ ግንኙነቷን እንደምታስቀጥል ያመላከተ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ለምታደርጋቸው የሁለትዮሽም ሆነ የባለብዙ ወገን ግንኙነቶች የሌሎችን ይሁንታ አትጠብቅም፡፡
አሁን ባለው የዓለም ስርዓት ከአንድ ጎራ ጋር ብቻ ከመቆም ይልቅ፤ ከሁሉም ጋር በመነጋገር የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ የዲፕሎማሲ ብስለት አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን በዚሁ ወቅት፤ ሁለቱ ሀገራት ሰባት አስርት ዓመታትን በተሻገረው ግንኙነታቸው በአጋርነት መዝለቃቸውን አውስተው፤ ግንኙነታቸው በአዳዲስ የትብብር መስኮች እየተጠናከረ እንደሚሄድ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሀገራቱ የብሪክስ አባል መሆናቸው በደቡብ ደቡብ ትብብርና በብሪክስ ማዕቀፍ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ተጨማሪ እድል ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ፔዜሽኪያን ጋር ያደረጉት ውይይት፤ የሀገራቱን የረጅም ዘመናት ግንኙነት ለማላቅ የሚያስችል መሆኑም ታምኖበታል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ

