Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከተሳታፊነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት ሚና የተሸጋገረው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብሯን በማሳደግና አህጉራዊ ሚናዋን በማጠናከር አዲስ የዲፕሎማሲ ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች፡፡
በዲፕሎማሲው ዘርፍ የምታደርገው የሰላም ጥረትና የልማት ትብብር፣ በአፍሪካ መድረክ ላይ እያሳየች ያለችው ተሳትፎ እና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ያላት ስትራቴጂካዊ ቦታ ለዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ከአህጉራዊና ከዓለም አቀፍ ትብብር ጋር በማስተሳሰር የውጭ ግንኙነቷን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረች ሲሆን፤ የብሪክስ አባልነትም የዚህ የዲፕሎማሲ ማንሰራራት ማረጋገጫ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው እያስመዘገበቻቸው ያሉ ታላላቅ ስኬቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት ስብስብ የሆነው የብሪክስ ሙሉ አባል መሆን መቻሏ በታሪኳ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳዩ በርካታ ስትራቴጂካዊ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የምትከተለውና መደመርን መሠረት ያደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከተጽዕኖ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ቀራጭነት እንድትሸጋገር አስችሏታል።
የመደመር መንግሥት የሚከተለው ዲፕሎማሲ ዓለምን በወዳጅና በጠላት የሚከፋፍል ሳይሆን፤ በጋራ ጥቅም የሚያስተሳስር ዲፕሎማሲ ነው።
በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው በ18ኛው የብሪክስ መሪዎች ጉባዔ ላይ የታየውም ይሄንን የሚያጠናክር የዲፕሎማሲ ስኬት ነው፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከተመልካች ወደ ተዋናይ፣ ከተሳታፊ ወደ አጀንዳ ቀራጭነት ሚና አሸጋግሯታል፡፡
በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም ከዓለም አቀፍ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና ገበያ ጋር በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር ያላትን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ይህ አቋም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከተለመደው የግንኙነት አድማስ በላይ እየሰፋ መምጣቱን የሚያሳይ ሲሆን፤ ዲፕሎማሲው ከፖለቲካዊ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚያዊ ዕድል መፍጠር፣ ከግንኙነት ወደ አጋርነት፣ ከአጋርነት ወደ የጋራ እሴት መፍጠር ተሸጋግሯል፡፡
‎በ18ኛው የብሪክስ የመሪዎቹ ጉባዔ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአባልና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ መስኮች ትብብር፣ በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች መክረዋል።
የኢትዮጵያ ድምጽ በተለያዩ የዓለም መድረኮች እየተሰማ መምጣቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አጀንዳ ቀረጻ ውስጥ ያላትን ሚና እያጠናከረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህም የዲፕሎማሲው ማንሰራራት ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ያላት ሚና እየተቀየረ ተሰሚነቷም እየጨመረ መምጣቱን አረጋግጧል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
Exit mobile version