አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም ተችሏል አለ የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን፡፡
የሐረሪ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሳሚ አብዱልዋሲ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ300 በላይ የሚሆኑ የጁገል የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እድሳት እና ልማት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል::
በከተማዋ የሚገኙ ሙዚየሞች እድሳት፣ የአባድር ፕላዛ እንዲሁም የጁገል ዙሪያ የአረንጓዴ ልማት እና የመናፈሻ ስፍራዎች ተገንብተው ለህዝብ ክፍት መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ከጁገል ውጪ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የቱሪስቶችን ፍሰት በመጨመር እና የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የ98 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ጠቅሰው፤ ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ32 በመቶ ልዩነት አለው ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር 98 በመቶ አፈጻጸም እንደነበር አንስተው፤ ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በ2018 በበጀት ዓመት በክልሉ የተገኙት 12 አዳዲስ የድንጋይ ላይ ጽሁፎች የቱሪዝም ሀብቱን ለማስፋት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸው፤ እነዚህ ጽሁፎች በተገኙበት ስፍራ በኤኮ-ቱሪዝም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በሆቴል እና እንግዳ ተቀባይነት ዘርፍ የነባሮቹን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ፤ ትላልቅ አልሚዎችን ወደ ክልሉ ማምጣት መቻሉን ጠቁመው፤ የኃይሌ ሆቴል እና ሪዞርት ቦታ ተረክቦ ግንባታ መጀመሩን እንደ አብነት ጠቅሰዋል::
በ2019 በጀት ዓመት በተያዘው ዕቅድ ሐኪም ጋራን ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ በተለይም ለሃይኪንግ ቱሪዝም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት፡፡
ጎብኚዎች ከጉብኝት ባሻገር የባህል ልውውጥ የሚያደርጉባቸውን የስነ-ጥበብ ስራዎችና ባህላዊ ውዝዋዜዎችን በራሳቸው በመሞከር ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው ፕሮግራሞች ተቀርጸው ወደ ስራ እንደሚገቡም አመልክተዋል፡፡
በመልካም ፈቃዱ

