Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የዋጋ ክብረወሰን አስመዘገበ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ስፔሻሊቲ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ከፍተኛ ተፈላጊነት የሚያረጋግጥ አዲስ ታሪካዊ የዋጋ ክብረወሰን አስመዝግቧል አለ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን፡፡
አንድ ኪሎ ግራም የጉጂ ቡና በ2ሺህ 376 ዶላር (በአሁኑ ምንዛሪ ወደ 380 ሺህ ብር ገደማ) በመሸጥ በሀገራችን የቡና ታሪክ ከፍተኛውን የዋጋ ደረጃ መያዙን ባለስልጣኑ ገልጿል።
ክብረወሰን በሆነ ዋጋ የተሸጠው ቡና የቴስቲ ኮፊ ባለቤት አቶ ፈይሰል አብዶሽ “ፈይሰል አብዶሽ ሲግኔቸር” በሚል ልዩ ስያሜ በበይነመረብ የስፔሻሊቲ ቡና ጨረታ ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀረቡት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
መቀመጫቸውን በእንግሊዝና አሜሪካ ባደረጉት ታዋቂው “ኤም ካልቲቮ” የበይነመረብ የጨረታ ማዕከል አማካኝነት የተካሄደው ይህ የሐራጅ ሽያጭ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የጥራት ማዕረግና የገበያ ተፈላጊነት በአዲስ መልክ ያስመሰከረ ሆኗል፡፡
ይህም የሀገራችንን የስፔሻሊቲ ቡና የገበያ መዳረሻዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማስፋት ትልቅ መንገድ የሚከፍት መሆኑን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከዚህ ታሪካዊ ጨረታ የተገኘው ሙሉ ገቢ በቴስቲ ፋውንዴሽን አማካኝነት በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ደንቢ ኡዶ ቀበሌ ለሚገነባው ዘመናዊ ጤና ጣቢያ ግንባታ ማስፈጸሚያነት ለበጎ አድራጎት ተግባር እንደሚውል ተገልጿል፡፡
ይህ በጎ አድራጎት የቡናውን ጥራት ለጠበቁት የጉጂ አርሶ አደሮችና ማኅበረሰብ የሚሰጥ ትልቅ ድጋፍና ምስጋና መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

Exit mobile version