Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሀገር የሚገነቡ ዜጎች የሚፈጠሩባቸው እንዲሆኑ እየተሰራ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ መስኮች ሀገር የሚገነቡ ዜጎች የሚፈጠሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እየተሰራ ነው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፡፡

‎የትምህርት ሚኒስቴር አዲስ ከተመደቡ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መምህራን ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም በኩል የወደፊቱ ሀገር የሚመሩ ዜጎች የሚፈልቁባቸው ተቋማት እንደሚሆኑ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
‎
‎ትምህርት ቤቶቹ የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ በሳይንስ፣ በፖለቲካ፣ በፍልስፍናና በሌሎች መስኮች ሀገር የሚገነቡ ሀገር ወዳድ ዜጎች መፍለቂያ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።
‎
‎ሁሉንም በእኩል በማገልገል ሀገርን ከችግር ማውጣት የሚችሉ ዜጎች የሚፈጠሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡
‎
በትምህርት ቤቶቹ የሚማሩት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ መምህራኑም ከተለያዩ አካባቢዎች በችሎታ የተመረጡ ናቸው ብለዋል።
‎
‎በፍጥነት እየተለወጠች በምትገኘው ዓለም ውስጥ ከጥገኝነት የተላቀቀች ሀገር መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመው፤ በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የተመደቡ መምህራን ተገቢውን እውቀት በማስተላለፍና በስነምግባር የማነጽ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

Exit mobile version