Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተቋማት ግንባታ የመደመር መንግሥት ቁልፍ ምሰሶ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማንኛውም ሀገር የፖለቲካ ሥርዓትና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከግለሰቦችና ከቡድን ፍላጎት በላይ የጸኑ እና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማትን መገንባት ፈታኝ ምዕራፍ ማለፍን ይጠይቃል።

በኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት መሪ ፍልስፍና ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የመደመር እሳቤ ከሚያስቀምጣቸው ቁልፍ ምሰሶዎች መካከል አንዱና ዋናው ተቋማትን መትከልና የማጽናት ተግባር ነው።

የመደመር መንግሥት ያለፉትን ሥርዓቶች ስብራትና የቢሮክራሲ ድክመቶች በመፈተሽ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገሩ ጠንካራና ተወዳዳሪ ተቋማትን ለመገንባት በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፤ አሁንም እያከናወነ ይገኛል።

ተደራራቢ የሥራ ኃላፊነት የነበራቸውን መሥሪያ ቤቶችን በማዋሃድ ተልዕኳቸውን በብቃት መወጣት የሚያስችል ቁመና እንዲኖራቸው እና ዘመኑን የዋጀ ምላሽ የመስጠት አቅም እንዲገነቡ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ ወጪ በመቆጠብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እንዲዘረጉ የተሰራው ስራ ውጤት አምጥቷል።

ያረጀውና ቀርፋፋው የመንግሥት መስሪያ ቤቶች አሠራር ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለሙስና የተጋለጠ በመሆኑ፣ የመደመር መንግሥት ተቋማትን የማዘመንና የመዋቅር ማሻሻያ ሥራዎችን በስፋት አከናውኗል።

ተቋማትን የመትከል እና የማጽናት ሂደት ጠንካራ፣ ዘላቂ እና ውጤታማ የሆኑ ድርጅቶችን ወይም የህዝብ ተቋማትን ለመገንባት የሚከናወን ስልታዊ ተግባር ነው። ይህ ሂደት በአንድ ማህበረሰብ ወይም ሀገር ውስጥ ህግና ስርዓትን ለማስከበር፣ አገልግሎትን ለማሻሻል እና እድገትን ለማምጣት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

መንግሥታዊ ተቋማትን የመትከል እና የማጽናት ሂደት በዋናነት ተቋማትን ነፃ፣ ጠንካራ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የማድረግ ስትራቴጂካዊ ተግባራትን ያካትታል። በመሆኑም የመደመር መንግሥት ቀደምት ድክመቶችን በማረም እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ላይ ትኩረት አድርጎ ሰርቷል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በርካታ ተቋማት የጸና ቁመና እንዲኖራቸው መደረጉን በአብነት ማንሳት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ ነፃ ሆኖ በገለልተኝነት እንዲደራጅ እና የሕዝብ አመኔታን እንዲያተርፍ ስለመደረጉ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት ማሳያ ነው።
የፍትህ ተቋማትም እንዲሁ ነፃ፣ ጠንካራ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ እንዲሆኑ መደረጉ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች ለማክበር በሚያስችል መልኩ አቅማቸውን አጠናክረው እየሰሩ ነው።

የመደመር መንግሥት ተቋማትን በመትከል እና በማጽናት ሂደት የሀገርን ሙሉ አቅሞች በጋራ ህልም በማስተባበር፣ ተቋማት ለአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ሳይሆን ለትውልድ እና ለዘላቂ ሀገር ግንባታ የሚቆሙበትን መሠረት ጥሏል፡፡

የቢሮክራሲውን ቀርፋፋነት ለመፍታት በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ለማድረግ የመሶብ አገልግሎት ወደ ተግባር ገብቶ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።
ተቋማትን የመትከልና የማጽናት ሂደት፣ በትናንት ስብራቶች ላይ ብቻ ከማልቀስ ወጥቶ፣ የዛሬን አቅም በማቀናጀት የወደፊቱን የሀገረ መንግሥት መሠረት የማጽናት ተግባር ነው። እነዚህ ተቋማዊ መሠረቶች የሀገሪቱን የነገ ዕጣ ፈንታ የተሳካ ለማድረግ ሚናቸው የጎላ ነው።

በትዕግስት ግዛቸው

Exit mobile version