አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ባሕር በር የውሃ አካል ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ንግድ የሚተነፍስበት ሕዝቦችን የሚያገናኝ የሉዓላዊነት ታላቅ መዳረሻ ነው።
ለቀይ ባሕርና ለኤደን ባሕረ ሰላጤ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ በታሪካዊ አሻጥሮች እና ሴራዎች ሳቢያ ለበርካታ ዓመታት ያለ ባሕር በር እንድትቀጥል ተገድዳለች።
ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለና የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ከንግድ የተሻገረ የብሔራዊ ደህንነት፣ የህልውና እና የኢኮኖሚ ምሰሶዋ ነው።
ታዲያ ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባሕር በር በማግኘት የጂኦግራፊ እስረኛ መሆኗ ማብቃት አለበት የሚል የጸና አቋም የያዘው የመደመር መንግሥት ይህንን የሕልውና ጥያቄ ለመመለስ ኃይልን ሳይሆን፤ ዲፕሎማሲን መሰረት አድርጓል።
በዚህም የጋራ ልማት፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና የንግድ ልውውጥን መሰረት ባደረገ የሰላም መንገድ መሄድ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
በሕንድ ኒውዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ታሪካዊና አንገብጋቢ አጀንዳ በአጽንኦት አንስተውታል።
በንግግራቸውም የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ከምንም በላይ ቀዳሚው እና እጅግ አስፈላጊው የኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ግዙፍ ኢኮኖሚና ብዙ ሕዝብ ላላት ሀገር አስተማማኝ የባሕር በርና ብዝሃ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች አስፈላጊነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ብሪክስ የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚችለው በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ፍትሃዊ ውሳኔ መስጠት ሲችል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድርጅቱ ለአባል ሀገራቱ እውነተኛ ዕድገትና የባለቤትነት መብት አጋር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በብሪክስ መድረክ ላይ በአጽንኦት ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ያመለከቱት ይህ የኢትዮጵያ አቋም፤ ኢትዮጵያ ጥያቄዋን በውይይት፣ በሰላም እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማሳካት የጀመረችው የዲፕሎማሲ ጉዞ እንደሚቀጥል ያረጋገጠ ነው።
በሶስና አለማየሁ

