አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማንኛውም ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ደህንነት እና ዘላቂ ሕልውና ውስጥ የጠንካራ ተቋማት ሚና የሚተካ አይደለም፡፡
የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ስኬታማ ሊሆንና አስተማማኝ መሰረት ሊይዝ የሚችለው በጠንካራ መዋቅር እና በጽኑ ተቋማዊ እሴቶች ላይ ሲገነባ ብቻ ነው።
ለአንድ ሀገር ዘላቂነት ወሳኙ የግለሰቦች ጊዜያዊ ሚና ወይም የፖለቲካ ሒደቶች መለዋወጥ ሳይሆን፣ ዘመናትን ተሻግረው ሀገርን እና ሕዝብን በታማኝነት ማገልገል የሚችሉ ተቋማትን እውን ማድረግ ነው፡፡
በተለይም የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደሙን ድርሻ የሚወስደው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ መልኩ ተደራጅቶ በትውልድ ተሻጋሪ እሴቶች ሲቀረፅ ለዘላቂ ሀገራዊ ሕልውና አስተማማኝ ዋስትና ይሆናል።
ሥርዓቶች እንዲሁም የፖለቲካ አስተሳሰቦች ሊቀየሩ ይችላሉ፤ ሀገር ግን በጽናት ትቀጥላለች። ይህንን ሀገራዊ ጽናት የማስጠበቅ ታላቅ ኃላፊነት ደግሞ በገለልተኝነት፣ በሙያዊ ብቃት እና በጽኑ መዋቅር ላይ በተገነባ ሠራዊት ትክሻ ላይ የሚወድቅ ሀገራዊ አደራ ነው።
በመደመር መንግሥት የተወሰዱ ቁርጠኛ ርምጃዎችና የተካሄዱ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊትን በዚሁ ዘመን ተሸጋሪ መሰረት ላይ ለማቆም ያለሙ ናቸው።
እነዚህ ጥረቶች ሠራዊቱ ከማንኛውም ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና ጊዜያዊ ፍላጎት በላይ ሆኖ፣ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት በብቃት ማስከበር የሚያስችለውን ተቋማዊ አቅም እንዲገነባ አድርገውታል።
የሪፎርሙ ዋና ዓላማ ተቋሙ ከየትኛውም ግለሰባዊ ወይም ሥርዓታዊ ፍላጎት በላይ ጸንቶ የሚቆምበትን ዘመናዊ አደረጃጀትና ሙያዊ ብቃት ማጎልበት ነው።
ይህም ማለት የፖለቲካ ወይም የሥርዓት ለውጥ በሚከሰትበት ወቅት እንኳን ተቋሙ ሳይናጋ ሀገርን የማጽናትና የሕዝብን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን በብቃት ይወጣል።
ተቋማት በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ፍላጎት ላይ ሳይሆን በሕግ በሙያዊ እሴት እንዲሁም በሀገርና ሕዝብ ፍቅር ላይ ሲመሰረቱ ትውልድ ተሻጋሪነታቸው እውን ማድረግ እንደሚችሉ የመከላከያ ሠራዊት ምስክር ነው፡፡
በመደመር መንግሥት በመገንባት ላይ ያለው ተቋማዊ አቅም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ባለፈ ለነገው ትውልድ የምትሻገር፣ የተረጋጋችና ሁለንተናዊ እድገቷ የተረጋገጠ ሀገርን እውን ለማድረግ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ አቅምና የውጊያ ጥንካሬውን የሚያረጋግጥ ብቻ ሳይሆን፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን ከሀገር ፍቅርና ሕዝባዊነት ጋር በመላበስ ለነገዋ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሕልውና አስተማማኝ የጽናት ምሰሶ ነው።
በመልካም ፈቃዱ

