አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታይም መጽሔት ባስነበበው ሰፊ ትንታኔ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ተልዕኮውን እውን ለማድረግ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረታዊ የኢነርጂ ማዕከል በመሆን የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክቷል።
አህጉራዊው ነፃ የንግድ ቀጣና ስርዓት ከአንድ ቢሊየን በላይ የሚሆነውን ሕዝብ እና ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብትን በማቀናጀት አፍሪካን ወደ አንድ የተቀናጀ የጋራ የኢኮኖሚ ገበያ የመቀየር ታላቅ ራዕይ ሰንቋል።
ይህንን ራዕይ በብቃት እውን ለማድረግ አስተማማኝ፣ ተወዳዳሪ እና አቅም ያለው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት መገንባት ግድ ይላል።
በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነጻ የንግድ ቀጣና ስርዓቱን ከሰነድነት አልፎ በተጨባጭ እውን ለማድረግ የጎላ ሚና እንዳለው ታይም መጽሔት ገልጿል።
እንደ መጽሔቱ ዘገባ፤ ግድቡ የአፍሪካ አህጉር የታዳሽ ኢነርጂ የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያገለግል ወሳኝ መሠረተ ልማት ነው።
አህጉራዊ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ዕድገት መፋጠን አነስተኛ ወጪ የሚጠይቅ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልገው ገልጾ፤ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የኃይል እጥረት እና በውድ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ምክንያት አምራች ኢንዱስትሪዎቻቸውን በሙሉ አቅም ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ፈተና የተጋረጠባቸው ሀገራት መፍትሔ እንደሚፈልጉ ጠቁሟል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨው ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ለምሥራቅ አፍሪካ እና ለአጎራባች ቀጣናዎች በስፋት ተደራሽ በመሆን ለፋብሪካዎች፣ ለትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ለሎጂስቲክስ አውታሮች ዋና የኢነርጂ ምንጭ ይሆናል ነው ያለው።
ይህም የምርቶችን የማምረቻ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ አፍሪካውያን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በከፍተኛ ጥራት ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንዲለዋወጡ መንገድ የሚከፍት መሆኑን በዘገባው አመልክቷል።
የሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ አንድነትን እና ቀጣናዊ ትስስርን በተግባር የሚያጠናክር መሆኑን ያነሳው ዘገባው፤ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከአንድ ሀገር ወደ ሌላው አህጉራዊ አካባቢ ማስተላለፍ የሀገራትን የኃይል ትስስር የሚያጠናክር እና የፖለቲካና የኢኮኖሚያዊ ትብብርን የበለጠ እንደሚያፋጥን አብራርቷል።
አፍሪካን በኢነርጂ እና በንግድ መሠረተ ልማት ማስተሳሰር አህጉራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስቶ፤ በዚህ ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሚና የላቀ እንደሆነ ገልጿል።
ግድቡ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ነፃነትና በራስ የመቆም ራዕይ ትልቅ አቅም ከመሆኑም በላይ፤ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ራዕይ እውን መሆን የኢነርጂ ዋስትና በመስጠት ወደ አዲስ የጋራ እድገት ምዕራፍ ለመሸጋገር ድልድይ እንደሚሆን ታይም መጽሔት በዘገባው አስነብቧል።
በአብረሃም አበራ

