አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ46 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን 12 የBYD Seagull ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በውክልና ለመሸጥ ከተረከበ በኋላ ገንዘቡን ለተበዳይ ሳያስረክብ ከባድ የማታለል ወንጀል ፈጽሞ ከሀገር የተሰወረው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ውሏል አለ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ።
ተጠርጣሪው ከግል ተበዳይ አቶ ዮናስ ገብረመስቀል ጋር በነበረው የውክልና ስምምነት ተሽከርካሪዎቹን ከተረከበ በኋላ፣ የተገኘውን ገንዘብ ይዞ ከሀገር በመውጣት በታይላንድ፣ በሲንጋፖር፣ በፊሊፒንስ እና በኢንዶኔዥያ ሀገራት ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ሲዘዋወር ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት (ኢንተርፖል) ጋር ባደረገው የቅርብ ትብብር በግለሰቡ ላይ ዓለም አቀፍ የቀይ ማስታወቂያ (Red Notice) እንዲወጣበት አድርጓል።
በዚህም መሠረት ተጠርጣሪው መስከረም 3 ቀን 2019 ዓ.ም በኢንዶኔዥያ ኢንተርፖል በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተላልፎ መሰጠቱ ነው የተገለጸው።
ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የምርመራ መዝገብ አደራጅቶ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም በሌሎች ሁለት ከባድ የማታለል ወንጀሎች ተጠርጥሮ ተጨማሪ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተለያዩ የሽብርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የሚፈለጉ አካላትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ ለማቅረብ ከሀገራት የፖሊስ ተቋማትና ከኢንተርፖል ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ለኢንዶኔዥያ ፖሊስ እና ለኢንተርፖል ምስጋናውን አቅርቧል።

