አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የብሪክስ ስብስብ አባል መሆኗ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ስትራቴጂካዊ ቦታ እና ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ከ40 በላይ ሀገራት የህብረቱ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበው ኢትዮጵያ በቅድሚያ የአባልነት ዕድል ማግኘቷ በዘመናዊው የጂኦፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ምህዳር ውስጥ ያላትን የላቀ ሚና እና ተጽዕኖ የሚያረጋግጥ ነው።
ይህ ስኬት በድንገት የተገኘ ሳይሆን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ፣ ያላትን የረጅም ጊዜ ፈር ቀዳጅነት ታሪክ የሚያንጸባርቅ ነው።
ኢገትዮጵያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የመንግሥታቱ ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽን) ብቸኛ ነጻ አፍሪካዊት አባል ሀገር በመሆን የሉዓላዊነት፣ የእኩልነት እና የፍትህ ድምጽ ሆና አገልግላለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ምስረታ የመሪነት ሚና የተጫወተች ሲሆን፤ በዚህ ሚናዋ አዲስ አበባን የአፍሪካ አህጉር የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ በቅታለች።
የብሪክስ አባል መሆኗ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ሁለገብ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስፋፋት እንዲሁም ከአዲሱ የልማት ባንክ የፋይናንስ አማራጮችን ለማግኘት ሰፊ መንገድ ይከፍትላታል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት፣ የህዝብ ብዛት እና በምስራቅ አፍሪካ ያላት የጂኦ ስትራቴጂካዊ መገኛ ለብሪክስ ህብረትም ቢሆን ከፍተኛ አቅም የሚያበረክት ነው።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት የታሪካዊ መሪነት ባለአደራነቷን ከዘመናዊው የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስር ጋር ያቀናጀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነት መድረኮች ላይ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የነጻነት ድምጽነቷን የበለጠ ያጠናክረዋል።
በአብረሃም አበራ

