Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ህብረትን የሰላም ጥረት የገፋው ሕገ ወጡ ህወሓት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይን ሕዝብ ለሁለንተናዊ ቀውስ እየዳረገ የሚገኘው ሕገ ወጡ ቡድን ህወሓት ከስሪቱ ጀምሮ ያለ ጦርነትና ሥልጣን መኖር የማይችል ጸረ ዴሞክራሲያዊ ስብስብ ነው፡፡

ሰላም ጠል የሆነው ሕገ ወጡ ሕወሓት በአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የቀረበውን የሰላም ጥረት በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በአፍሪካ ህብረት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ እና በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ የረጅም ጊዜ የካበተ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡

ኦባሳንጆ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኳቸውን ለመወጣት እና በአህጉሪቱ ካላቸው የካበተ የፖለቲካ ልምድ አንፃር ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ካሰበው የጥፋት ተልዕኮ እንዲታቀብ በተደጋጋሚ ለሽምግልና ወደ መቐለ አቅንተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ያለ ጦርነት ሕልውናውን ማቆየት የሚችል የማይመስለው ሕገ ወጡ ህወሓት የኦባሳንጆን የሰላም ጥሪ «ገለልተኝነት እና ግልጽነት የጎደለው ነው» ሲል ተችቷል፡፡

ቡድኑ ላቀረበባቸው መሰረተ ቢስ ክስ መልስ የሰጡት ኦባሳንጆ÷ ከሰላም ተልዕኮ ውጭ ሌላ ዓላማ እንደሌላቸው በመጥቀስ የሕገወጡ ህወሓት ትችት መሰረተ ቢስ እና ቡድኑ ለሰላም ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለው ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሲፈረም የቡድኑ አመራሮች በኦባሳንጆ የድርድር ሃሳቦች ተስማምተው እንደነበር አስታውሰው÷ ነገር ግን አሁን ላይ አንዳንድ የህገወጡ ህወሓት አመራሮች ኦባሳንጆ በፕሪቶሪያው ስምምነት ወቅት ያደረጉትን ጥረት ሲያጣጥሉ መሰማታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሕገ ወጡ ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለው በተደጋጋሚ ያረጋገጠ ሲሆን÷ አሁን ላይ ተዋጊ ኃይሉን መልሶ በማደራጀት የጦርነት ጉስማ እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህ ሕገ ወጥ ቡድን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የአፍሪካ ህብረት ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለው ያሳኩትን የፕሪቶሪያ ስምምነት መጣሱ ቡድኑ ለሰላማዊ ንግግርም ሆነ ለሰብዓዊ እሴቶች ደንታ እንደሌለው የሚያሳይ ነው።

ቀደም ሲል ሕወሓት በሀገር ውስጥ የተደረጉ የሽምግልና ጥረቶችን በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ቡድኑ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ ከአውሮፓ እና አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በማን አለብኝነት ገፍቷል፡፡

በታሪኩ ልዩነቶችን በውይይት ፈትቶ የማያውቀው ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ፍላጎት የለውም። ሕዝቡን ለዳግም ጦርነትና እልቂት ለመዳረግ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ጭምር ህብረት እየፈጠረ ይገኛል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላምና ልማት የሚያስፈልገው በመሆኑ ሕገ ወጡ ቡድን ከደቀነበት የጦርነት አደጋ ለመታደግ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version