አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስገኙ ነው አለ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ ተረፈ እንዳሉት÷የክልሉን የግብርና ዘርፍ ውጤታማነት ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የግብርና ፖሊሲና የተጠቃሚዎች ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ፣ ማበልጸግና ማለማመድ ላይ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የክልሉን የግብርና ምርምር ፈጣን፣ ውጤታማ፣ የልማት ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የሚያስችል አቅም መገንባት እና ሥርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በሒደቱ የወጡ ውጤቶችን ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ ማድረግና የማስታወቅ ሥራዎችን መሥራት ዋናው የኢንስቲትዩቱ ዓላማ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት 69 ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና 210 የምርምር አጀንዳዎችን በማዘጋጀት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት፡፡
በዛሬው ዕለትም በኢንስቲትዩቱ የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል የማሕበረሰብ አሳታፊ የበጎች አውራ መረጣና ሥርጭት የባለድርሻ አካላት የመስክ ምልከታ መካሄዱን አንስተዋል፡፡
የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ቀድራላ ዋበላ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በማዕከሉ የግብርና ምርት እድገት ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችሉ ከ195 በላይ የምርምር ሥራዎች በመሥራት የተገኙ ቴክኖሎጂዎችን የማስረጽ ሥራ በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የእንስሳትና የዶሮ ዝርያዎችን የማሻሻልና የማላመድ እንዲሁም የተለያዩ የመኖ ዝርያዎችን የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

