አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የቀዳማይ ልጅነት ልማትን በማጠናከር ለሕፃናት የተሻለ የእድገት አካባቢ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው አሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)።
የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል በባሕር ዳር ከተማ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ሥራዎችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የክልሉ ተቋማት ጋር ምክክር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ትውልድ ግንባታ የሚጀምረው ልጆች ካደጉ በኋላ ሳይሆን እድገታቸው ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በመሆኑ ለቀዳማይ ልጅነት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።
ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ለሕፃናት እንክብካቤ መስጠት፣ የተሟላ የአመጋገብ ሥርዓትን መተግበር፣ የመዋያ፣ መማሪያና መዝናኛ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት እንዲሁም ለሕፃናት የተሻለ የእድገት አካባቢ መፍጠር ላይ የክልሉ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ሥራ አስፈጻሚ መሠረት ዘለዓለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቀዳማይ ልጅነት ልማት እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ባሉ ሕፃናት ላይ ትኩረት በማድረግ ለአእምሮ እድገትና ለአካላዊ ጤንነት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮችን ለማሟላት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅድመ ጽንስ የእናቶች ጤና ጀምሮ ከወሊድ በኋላ የጨቅላ ሕፃናት እንክብካቤን ጨምሮ የሚከናወነው የቀዳማይ ልጅነት ልማት በኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የፖሊሲ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በተለያዩ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የቀዳማይ ልጅነት ልማት ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የትምህርት፣ ጤና፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ እንዲሁም የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮዎች በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል መንግሥት የቀዳማይ ልጅነት ልማት መረጃ መሰብሰቢያ ሶፍትዌር አገልግሎት ማስጀመሩና ማስተዋወቁም ተገልጿል።
ሶፍትዌሩ ተቋማት በቀዳማይ ልጅነት ልማት የሚያከናውኗቸውን ሥራዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርተው እንዲፈጽሙ ከማስቻሉ ባሻገር ውጤታማ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ያግዛል ተብሏል።
በደሳለኝ ቢራራ

