Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ በብሪክስ ጉባዔ ዋነኛዋ ሻምፒዮን ናት – የቻይና ዲፕሎማት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ቻይና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጸና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትና አመራር በበርካታ የትብብር ማዕቀፎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው አለ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ተጠባባቂ ዋና ኃላፊ ሰን ሚንግሺ በኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት፣ በብሪክስ ትብብርና በቻይና አቋም ዙሪያ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሰን ሚንግሺ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያና ቻይና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

በቅርቡ በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሔደው 18ኛው የብሪክስ ጉባዔ ላይ ትልቅ ድል ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ መሆኗን አውስተዋል፡፡

ለአብነትም ከብሪክስ አባል ሀገራት ለዓለም ንግድ ድርጀት አባልነት ሒደት፣ ለዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የአፍሪካ ብቸኛ ዕጩነቷ እና ለኮፕ 32 ጉባዔ ሙሉ ድጋፍ ማግኘቷን ጠቅሰዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2023 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቤጂንግ ባደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት ከፕሬዚደንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ያደረጉት ውይይት÷ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ወደ ማይበገር ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዲሸጋገር ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህ ውሳኔ በመሠረተ ልማት፣ በንግድ እና ሎጂስቲክስ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም በታዳሽ ሃይል እና በሕዝብ ለሕዝብ የትብብር ዘርፎች ሰፊና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ነው ያብራሩት።

የመሠረተ ልማት ትብብርን በተመለከተ በቻይናው የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት የተገነባውና ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የኢትዮ-ጅቡቲ የንግድ ኮሪደር የጀርባ አጥንት ሆኖ ማገልገል መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም በሶማሌ ክልል በቻይናው የግንባታ ተቋራጭ ድርጅት የተገነባው እና 120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ትልቁ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ሆኖ ሥራ መጀመሩን አንስተዋል፡፡

በንግድ እና ሎጂስቲክስ ትስስር ረገድም ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላላቸው 53 የአፍሪካ ሀገራት ያደረገችው ከቀረጥ ነፃ የንግድ መመሪያ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው ያስረዱት፡፡

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ወደ ቻይና ገበያ በስፋት ከሚላኩ ምርቶች መካከል ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን ÷ ባለፈው ነሐሴ ወር በአዲስ አበባ በተካሄደው የንግድ መድረክ ከ330 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው ስምምነቶች መፈረማቸው ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቼንግዱ-አዲስ አበባ የካርጎ በረራ መስመር መጀመሩ የንግድ ልውውጡን ይበልጥ ማቀላጠፉን ሰን ሚንግሺ ተናግረዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ ለማጠናከር በቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ስልጠናዎች፣ በግብርና ባለሙያዎች የሙያ ልውውጥ እና በልዩ ልዩ ስልጠናዎች ላይ ሰፊ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

ከፈረንጆቹ 1974 ጀምሮ ሳይቋረጥ በኢትዮጵያ እየሰሩ የሚገኙት የቻይና የሕክምና ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት መታደጋቸውን ጠቅሰው ÷ በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የቀዶ ጥገና ሮቦትና የኢንዶስኮፒ ማሰልጠኛ ማዕከል ለቀጣናው ሀገራት ባለሙያዎች የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ማዕከል ነው ብለዋል፡፡

በአዳዲስ የትብብር መስኮች ረገድም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትብብር ድርጅት መሥራች አባል መሆኗ ሀገሪቱ ከዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ጋር በሚዛመዱ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክረ ጠቁመዋል።

የሁለቱ ሀገራት የሁለዮሽ ትስስር በብሪክስ፣ በቻይና-አፍሪካ ትብብር እና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች አማካኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለዚህም ሀገራቸው ጽኑ አቋም ያላት መሆኑን ዲፕሎማቱ በማብራሪያቸው አረጋግጠዋል።

በመሳፍንት ብርሌ

Exit mobile version