አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ቀንድ ኤልኒኖ ሊያስከትለው የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም በመዘጋጀት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ሥርዓቷን በቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ በስጋት ፋይናንስ እና በቅድመ መከላከል እርምጃዎች ዙሪያ እያጠናከረች ነው።
ኢጋድ በአፍሪካ ቀንድ ኤልኒኖ የሚያስከትለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የሚያደርጉትን ዝግጅት በተመለከተ በአዲስ አበባ ምክክር አካሂዷል።
የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ ቀንድ ኤልኒኖ ሊያስከትል የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያና የቅድመ ትንበያ እርምጃ መውሰድ አለባቸው።
ኤልኒኖ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ የመቋቋም የቴክኒክ ዝግጁነት ከፖለቲካ አመራር፣ ከሀገራዊ ባለቤትነት፣ ከቀጣናዊ አስቸኳይ ፋይናንስ እና ከቅድመ እርምጃዎች ጋር ሊጣመር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኤልኒኖ ክስተት በአፍሪካ ቀንድ በሕይወትና በንብረት ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመው፤ በተለይም ከወትሮው የተለየ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊያስከትል እንደሚችል ተመልክቷል ብለዋል።
የኤልኒኖ መከሰት ተፈጥሯዊ መሆኑን በማንሳት፣ የዝናቡ መጠን በግብርና፣ በእንስሳት እርባታ እና በምግብ ዋስትና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ለዚህ ደግሞ ኤልኒኖ በአፍሪካ ቀንድ ሊያስከትለው የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም የቀጣናው ሀገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ቅድመ ትንበያ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ከ24 ሰዓታት በፊት ማድረስ ብቻ የአደጋውን መጠን በ30 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ለቅድመ ዝግጅትና ቅድመ ትንበያ እርምጃዎች ከወዲሁ የድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ወጪን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የኢጋድ አባል ሀገራት ዕቅዶቻቸውን ማቅረብ፣ ግብዓቶችን አስቀድመው ማከማቸትና ድንበር ተሻጋሪ የማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ማጋራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር እድሩስ ሀሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ኤልኒኖ ሊያስከትል የሚችለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም እየሰራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ሥርዓቷ ዘርፈ ብዙ አደጋዎችን የሚከላከል፣ በጉዳት ትንበያ ላይ የተመሰረተ፣ ቅድመ መከላከልን ማዕከል ያደረገ እና ሁሉንም ዘርፎች ያካተተ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ይህም በክትትል፣ በትንበያ፣ በጉዳት ግምገማ፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ በዝግጁነት፣ በቅድመ መከላከል እርምጃዎች እና በምላሽ አሰጣጥ መካከል ያለውን ቁርኝት ያጠናክራል ብለዋል።
ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት እና አቅሞች በአደጋ ዝግጁነት ማዕከል ሊሆኑ እንደሚገባቸውና ሰብአዊ ምላሾች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድጋፎች የሀገሪቱን አመራርና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ሊደግፉ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ዝግጁነትን፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያን፣ የቅድመ መከላከል እርምጃዎችን፣ ምላሽን እና የማቋቋም ሥራዎችን ጨምሮ ለአደጋ ስጋት አመራር አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢጋድ አባል ሀገራት አደጋዎች ከደረሱ በኋላ ሳይሆን ከመከሰታቸው በፊት ሀብት ዝግጁ እንዲሆን የሚያስችሉ ሀገራዊ የአደጋ ስጋት ፋይናንስ ሥርዓቶችን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአደጋ ስጋቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሳሰሩ እና ድንበር ተሻጋሪ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸው፤ በድንበር ተሻጋሪ መረጃ ልውውጥ፣ በጋራ የስጋት ትንተና፣ በተቀናጁ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች እና በተቀናጀ የቅድመ መከላከል እርምጃዎች አማካኝነት ጠንካራ ቀጣናዊ ትብብር እንዲኖር ጠይቀዋል።

