Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ከ1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን በምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2019 ዓ.ም ከ1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን በምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጀንሲ።

የኤጀንሲው ምትክል ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩ የህጻናትን ትምህርታዊ ውጤት፣ ስነምግባር እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለማሻሻል የሚያስችሉ አጠቃላይ ስራዎችን በማከናወን ላይ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ የምገባ መርሃ ግብር አንዱ ነው።

በዚህም በ2019 ዓ.ም ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም ትምህርት ቤቶችን ለምገባው ምቹ ለማድረግ የመሰረተ ልማት ቅድመ ዝግጅቶች፣ የመጋቢ እናቶች የጤና ምርመራ እና የበጀት ማዕቀፍ የማዘጋጀት ስራዎች መሰራታቸውን አመልክተዋል።

የምገባ መርሐ ግብሩ ከተማሪዎች ውጤት መሻሻል ባሻገር፤ የተማሪዎች ማርፈድ እና ከትምህርት ገበታ መቅረት እንዲቀንስ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።

መርሐ ግብሩ የወላጆችን የኢኮኖሚ ጫና በማቃለል በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ከ4 ሺህ እስከ 6 ሺህ የሚደርሱ እናቶችም የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው አስረድተዋል።

የምገባ መርሐ ግብር የልጆችን የመማር እና ምግብ የማግኘት መብት ከማረጋገጥ ባለፈ የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በምገባ በሂደቱ የዋጋ ግሽበት ተግዳሮትን ለመቋቋም ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version