Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አሜሪካ በቻይና ዲፕሎማቶች ላይ የጉዞ ክልከላ ማዕቀቦችን ጣለች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ በቻይና ዲፕሎማቶች ላይ የጉዞ ክልከላ ማዕቀቦችን መጣሏን አስታውቃለች።

በዚህም መሰረት ከፍተኛ የቻይና ዲፕሎማቶች የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመጎብኘት አሊያም ከ50 ሰው በላይ የሚሳተፍበት ባህላዊ ስነ ስርዓቶች ላይ ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ካሰቡ መጀመሪያ ከሀገራቸው ከመነሳታቸው በፊት ፍቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

ዋሽንግተን የጉዞ ክልከላ ማእቀቡን ያወጣችው ቤጂንግ በቅርቡ በአሜሪካ ዲፕሎማቶች ላይ ክልከላዎችን መጣሏን ተከትሎ እንደሆነም ተነግሯል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፥ የሁሉም የቻይና ኤምባሲ እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ አድራሻዎች ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ መሆኑን ለመለየት ይሰራል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፖምፒዮ፥ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በቻይና የሚያገኙት አገልግሎት በአሜሪካ ላሉት የቻይና ዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ መሰረት ነው ብለዋል።

በአሜሪካ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በበኩሉ፥ በቻይና ዲፕሎማቶች ላይ የተጣለው የጉዞ ክልከላ ምክንያታዊ ያልሆነ እርምጃ ነው ሲል አጣጥሎታል።

ምንጭ፦ reuters.com

Exit mobile version