አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 28 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኮቪድ 19 ወረርሽኝ 47 ሚሊየን የሚሆኑ ተጨማሪ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ወደ ድህነት ሊያስገባ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠነቀቀ።
ሴቶች በአብዛኛው መደበኛ ባልሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ የመሥራት ዕድላቸው ሰፊ ከመሆኑም ባለፈ በወረርሽኙ በጣም በተጎዱና ለረዥም ጊዜ በተዘጉ ዘርፎች ላይ በመሰማራታቸው ከወንዶች በበለጠ በፍጥነት ሥራቸውን ማጣታቸው ተገልጿል።
ይህም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የድህነት ልዩነት ያሰፋ ሲሆን ÷እስከ ሚቀጥለው ዓመት ድረስ 47 ሚሊየን ተጨማሪ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ወደ ድህነት ሕይወት ውስጥ ያስገባቸዋል ተብሏል።
ከዚያም ባለፈ በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ የተገኘውን እድገት ይቀለብሳልም ነው ያለው ድርጅቱ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ሃላፊ ፉምዚሌ ምላምቦ-ንግኩካ በሰጡት መግለጫ ÷ በሴቶች ላይ እጅግ የከፋ ድህነት መጨመር ማህበረሰባችንን እና ኢኮኖሚያችንን የገነባንባቸው መንገዶች ላይ ጥልቅ ጉድለቶች መኖራቸውን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በዚህም በአለም አቀፉ ደረጃ በኮቪድ 19 በተፈጠረው የኢኮኖሚ ውድቀት እና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ መደበኛ ባልሆኑ ሠራተኞች ላይ ባስከተለው ከፍተኛ የሥራ ማጣት ምክንያት ከወንዶች የበለጠ ሴቶችን ለከፋ ድህነት አጋልጧል ነው የተባለው።
ምንጭ፡- አልጀዚራ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

