Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመስከረም ወር ከሚከበሩ በዓላት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመስከረም ወር ከሚከበሩ በዓላት ከ7 መቶ ሺህ በላይ እንግዶች እና ከ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ይጠበቃል አለ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፥ በክልሉ ዓመቱን ሙሉ ከ40 እስከ 50 የሚደርሱ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት ሲከበሩ በመስከረም ወር ብቻ አራት በዓላቶች ይከበራሉ።
በመስከረም ወር የሚከበሩት በዓላትም ፥ የመስቀል በዓል ፣ የሐዲያ የዘመን መለወጫ በዓል ያሆዴ ፣ በከምባታ ጠንባሮ እና ዶንጋ ማህበረሰብ የሚከበረው የመሳላ በዓል እና የየም የዘመን መለወጫ በዓል ሄቦ ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።
እነዚህን በዓላት በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንና ከ670 ሺህ እስከ 740 ሺህ እንግዶች በዓሉን ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በበዓላቱ ወቅት በሚኖረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ነው ያሉት።
ኃላፊው ከትራንስፖርት ፣ከማረፊያ ስፍራዎች እና ከሌሎችም አስፈላጊ ሁኔታዎች አንጻር ዝግጅቶች መከናወናቸውና እንግዶች ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን በዓላቱን እንዲያከብሩ የኮሚኒቲ ቤዝድ የእንግዳ አቀባበል ስርዓት መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።
በእመቤት ሲሳይ
Exit mobile version